ጥንታዊቷ የኡዝቤኪስታን ከተማ ሳማርካንድ በሰማያዊ ጉልላቶቿና በታሪካዊ የንግድ ጎዳናዎቿ መካከለኛው እስያን ከዓለም ጋር ስታገናኝ እንደነበረች ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ በመጠቀም የአህጉሪቱ አቋራጭ የትስስር መስመር ቁልፍ ተዋናይ ሆና ብቅ ብላለች።
በጥንት ዘመን በበረሃና በተራራ ውጣ ውረዶች በግመልና በፈረስ ይጓጓዙ የነበሩ የንግድ ሸቀጦች፤ ዛሬ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው በዘመናዊ የባቡር፣ የመርከብና የአየር ትራንስፖርት በመጠቀም አገራትን ወደተሻለ የጋራ ዕድገት እያሸጋገሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ሰፊ የሀገር ውስጥ ገበያ አቅሟን፣ የበለፀገ የግብርና ምርቷንና የዓለም አቀፍ አየር መንገድ መዋቅሯን በማቀናጀት ከእስያ አገራት በተለይም ከቻይና እና ከመካከለኛው እስያ ጋር ያላትን የንግድና የልማት ትስስር ወደ አዲስ ደረጃ አሳድጋዋለች።
ኡዝቤኪስታን በመካከለኛው እስያ የሚገኙ አገራትን ከቻይናና ከሌሎች ገበያዎች ጋር ለማገናኘት የባቡርና የመንገድ ኮሪደሮችን እያስፋፋች እንደሆነ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የምስራቅ አፍሪካ የንግድና የሎጂስቲክስ መገናኛ ማዕከል ለመሆን አቅሟን በጥንካሬ እያጎለበተች ነው።
ከጅቡቲ ወደብ ጋር ያለው የባቡርና የመንገድ ትስስር፣ የአዲስ አበባ የአየር ትራንስፖርት መነሻነትና የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ኢትዮጵያን በአህጉራዊ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ የማይተካ ሚና እንድትጫወት አስችሏታል።
የዚህ አህጉር አቋራጭ ትስስር ዋና ዓላማ የትራንስፖርት አውታሮችን ማደስ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን፣ ገበያዎችን፣ እውቀትንና ምርትን ማገናኘትን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ቡና፣ ሰሊጥና አበባ ያሉ ምርቶቿን ለዓለም ገበያ በተሻለ ዋጋ ከመሸጥ ባሻገር ከእስያ የሚመጡ የቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንትና የልምድ ልውውጦችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሰፊ መደላደል ፈጥራለች።
ከሳማርካንድ ጥንታዊ ታሪክ እስከ አዲስ አበባ ዘመናዊ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከላት የሚዘልቀው ይህ ድንቅ አቅጣጫ አህጉራትን የሚያገናኝ አዲስ የትስስር ስዕል ይስላል።
ኡዝቤኪስታን በመካከለኛው እስያ፣ ቻይና በእስያ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላቸውን ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ በማጣመር ንግድን፣ ባህልንና ልማትን የሚያገናኝ አዲስ የትብብር ዘመን እያበሰሩ ይገኛሉ።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የዚህ አዲስ ዓለም አቀፍ የንግድና የባህል ትስስር ታሪክ ተመልካች ብቻ ሳትሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ የራሷን የልማትና የበላይነት ምዕራፍ በድምቀት እየጻፈች ያለች ታላቅ ተዋናይ ናት።
በስምረት ገዛኸኝ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: