በዓለማችን ባሉ ትላልቅ ፓርቲዎች የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ "ፓርቲ እና ሕዝብ አንድ ናቸው" የሚል አስተሳሰብ ከእውነት የራቀና በምሁራንም ሆነ በተመራማሪዎች ዘንድ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን የወለዶ ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጉዕሽ ግደይ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኋላቀሩ የህወሓት ቡድን ይህንን ማደናገሪያ ሴራ በመጠቀም የትግራይን ሕዝብ ለፖለቲካ ሸፍጥ መጠቀሚያ ሲያደርገው መቆየቱን ጠቅሰው፣ ይህ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ከሥር መሰረቱ ተነቅሎ መጥፋት እንዳለበት አብራርተዋል።
የቡድኑ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አፋኝ ርዕዮተ ዓለም ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳያቆጠቁጡና አዳዲስ ሀሳቦች እንዳይፈጠሩ ለማፈን የሚያገለግል የፖለቲካ ሴራ ነው።
በዓለም ታሪክ የትኛውም ርዕዮተ ዓለምና ፓርቲ እንደ ሰው ተወልዶ፣ አድጎና አርጅቶ የሚሞት ሲሆን፤ ሕዝብ ግን በትውልድ ሰንሰለት ተሳስሮ ከዘመን ወደ ዘመን የሚሸጋገር ነባር ነው።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ መንግሥታት እና ፓርቲዎች አልፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸንቶ እንደሚቀጥለው ሁሉ፣ ፓርቲና ሕዝብ እኩል ነው የሚለው የበሰበሰ አስተሳሰብ መጪው ትውልድ በራሱ አዲስ ሀሳብ እንዳይመራ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ግን ይህ ሴራ በመክሸፉ ሕዝቡ ተደራጅቶ እየታገለው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ትግራይ አሁን የሚያስፈልጋት ትውልድን የሚያሻግርና ሕዝብን ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል አዲስ ሀሳብ ነው።
ይሁን እንጂ ለለውጥ ዝግጁ ያልሆነው አፋኙ የህወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ ጥያቄዎች በተሳሳተ መንገድ በመምራት ሕዝቡን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ይህ ቡድን ለሰላም፣ ለልማት እና ለአንድነት ያልቆመ፣ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት ብቻ የሚጠቀምበት የከሰረ ስብስብ መሆኑንም መላው ሕዝብ ነቅቶበታል።
ዴሞክራሲን አስፍናለሁ እያለ ሕዝብን የሚያፍን እና የሚገድል፣ እንዲሁም የፍትህ ሥርዓቱን በፖለቲካ ሴራ የተቆጣጠረ የቤተሰብ ስብስብ መሆኑንም በተግባር አሳይቷል።
በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ ቀንና ሌሊት እየተፍጨረጨረ ይገኛል።
ለዚህም ዋነኛ ማሳያው ‘ፅምዶ’ የተሰኘ ሕገወጥ ጥምረት ፈጥሮ በግልጽ እየሰራ መሆኑ ነው። ይህ የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይወክል ጫፍ የረገጠ ክህደት ሲሆን፤ በዚህ ሕገወጥ እንቅስቃሴውም የትግራይ ወጣቶችን በኃይል እያፈነ ወደ ሱዳን በዶላር እየሸጣቸው ይገኛል።
በወጣቶች ላይ የሚፈጸመው ግፍ ለቡድኑ ምንም ትርጉም ባይሰጠውም፤ ሕዝቡ ግን ለዚህ ሕገወጥ ተግባር "ይብቃን፣ ሰላም ስጡን፣ እምቢ ለጭቆና" በማለት ድምጹን እያሰማ ነው።
ትግራይ በኢትዮጵያ ሕገመንግስት የምትተዳደር ክልል በመሆኗ ከፌዴራል መንግስት እውቅና ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት ተቀባይነት የሌለውና የመጨረሻ ክህደት ነው።
ሥልጣኑን ለማስቀጠል ዳግም ጦርነት ለመለኮስ የሚዘጋጀው እና ሕጋዊ ሰውነት የሌለው ይህ ቡድን እያደረገ ያለው የጦርነት ትንኮሳ፣ የትግራይ ሕዝብ ዕውቅና የሌለው መሆኑን ሁሉም የሚመለከተው አካል ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም ትግራይ የኢትዮጵያ መሰረት መሆኗን ገልጸው፤ አባቶቻችን ያስተማሩን ኢትዮጵያዊነትን መሆኑን አስታውሰዋል።
ተጋሩ ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል፤ በመሆኑም ኋላቀሩ የሕወሓት ቡድን የትኛውንም ትግራዋይ ኢትዮጵያዊነቱን ሊነጥቀው አይችልም ሲሉ አብራርተዋል።
ሕገወጡ ቡድን እየተከተለው ያለው የጥፋት መንገድ የትግራይን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሕዝብ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊያውቀው ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በጎሳዬ ገ/ኪዳን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: