ኢትዮጵያ "የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ" የሚል ስም ተሰጥቷት ለዘመናት ስትጠራበት ኖራለች። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች ባደረጓቸው ንግግሮች በግልጽ እንዳስገነዘቡት፣ ይህ የውኃ ማማነት ስያሜ ኢትዮጵያውያን የውኃ ሀብት እንዳላቸው እያሰቡ በተግባር ግን በውኃ ጥም እንዲኖሩ የተፈጠረ የረቀቀ ማዘናጊያ ትርክት ነው።
ይህ ስያሜ እውነተኛውን የተፈጥሮ ጸጋ የሚያንጸባርቅ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ወንዞቿን ገድባ ከመጠቀም ይልቅ ውኃውን ሳታቁር ለታችኛው ተፋሰስ ብቻ እንድታስረክብ የተጠነሰሰ የፖለቲካ ሴራ ሆኖ ቆይቷል።
ትርክቱ ሕዝቡን በማዘናጋት ሌሎች በተፈጥሮ ሀብታችን ሲለሙ እኛ ግን በድርቅ እና በድህነት አዙሪት ውስጥ እንድንቆይ አድርጎናል።
ጋዜጠኛ እና ደራሲ ስለባት ማናዬ መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በ'ግሎባል ሪሰርች' ላይ አሳትሞ ሰሞኑን ዳግም ባጋራው ጥናት እንዳስቀመጠው፣ የዓባይ ወንዝ ጂኦ-ፖለቲካ ለዘመናት የታችኛው ተፋሰስ ተጋሪዎችን ፍትሐዊ ያልሆነ የበላይነት ያጎናጸፈ እና የላይኞቹን ደግሞ የመልማት መብት የገደበ የታሪክ አውድማ ሆኖ አልፏል።
የዚህ ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊነት ዋነኛ መነሻ ደግሞ ብሪታንያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ የራሷን እና የቅኝ ግዛቶቿን ጥቅም ለማስጠበቅ የዘረጋቻቸው አድሎአዊ የሕግ ማዕቀፎች ናቸው።
እ.አ.አ የ1891 የሮም ውል፣ በ1902 በብሪታንያ እና በዳግማዊ አጼ ምኒልክ መካከል የተደረገው አሻሚ ስምምነት፣ የ1906 የሦስትዮሽ ውል፣ እንዲሁም ግብጽ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ የ"ቬቶ" መብት እንዲኖራት ያደረገው የ1929 ውል የዚህ ተጽዕኖ ማሳያዎች ናቸው።
ይህ የፖለቲካ እና የሕግ ጫና እ.አ.አ በ1959 በግብጽ እና በሱዳን መካከል በተፈረመው የውኃ ክፍፍል ስምምነት ላይ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። ስምምነቱ ከዓባይ 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ዓመታዊ ፍሰት ውስጥ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለግብጽ፣ 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለሱዳን የሰጠ ነበር።
የቀረውን 10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ደግሞ ለትነት በመተው የውኃውን ትክክለኛ ባለቤት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ያገለለ ነበር። ኢትዮጵያም ይህንን የዜሮ ድምር ጨዋታ በፍጹም ሳትቀበለው ዘመናት ተቆጥረዋል።
በጥናቱ መረጃ መሠረት እ.አ.አ በ2020 ኢትዮጵያ የ114.9 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ስትሆን፣ ግብጽ 102.3 ሚሊዮን እንዲሁም ሱዳን 43.8 ሚሊዮን ሕዝብ ነበራቸው። በወቅቱ በነበረው መረጃ መሠረት በግብጽ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መቶ በመቶ እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት 99 በመቶ ደርሶ ነበር።
በኢትዮጵያ በኩል ግን የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ 44.3 በመቶ እንዲሁም የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነቱ 41 በመቶ ብቻ ነበር። በተመሳሳይ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ የንጹሕ ውኃ አጠቃቀም በግብጽ 923 ሜትር ኪዩብ፣ በሱዳን 807 ሜትር ኪዩብ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ 72 ሜትር ኪዩብ ብቻ መሆኑ ኢ-ፍትሐዊነቱን በጉልህ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ130 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ደግሞ የሕልውና እና የልማት ጥያቄውን ፈጽሞ የማይታጠፍ ያደርገዋል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብጽ እና ሱዳን አማራጭ የውኃ ሀብት የሌላቸው በማስመሰል የሚያቀርቡት መከራከሪያ ሳይንሳዊ መሠረት የለውም። ሁለቱ ሀገራት በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ የከርሰ ምድር ውኃዎች አንዱ የሆነው እና 150 ሺህ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይይዛል ተብሎ የሚገመተው የ"ኑቢያን ሳንድስቶን" (Nubian Sandstone Aquifer System) የከርሰ ምድር ውኃ ክምችት ባለቤቶች ናቸው።
ግብጽ ከዚህ ሀብት 10 በመቶውን እንኳን ብትጠቀም ለሁለት ምዕተ ዓመታት የሚሆን በቂ ውኃ ማግኘት እንደምትችል የዘርፉ ምሁራን ያረጋግጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ውኃን የማጣራት ሰፊ አማራጭ እያሏት በዓባይ ላይ ብቻ የሙጥኝ ማለቷ፣ ፖለቲካዊ የበላይነትን ለማስቀጠል የሚደረግ ሴራ መሆኑን ያጋልጣል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በከፍተኛ የዝናብ መበታተን እና በአስቸጋሪ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ምክንያት በተግባር ማልማት የምትችለው የውኃ መጠን 13 በመቶ ወይም 124 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው።
የዓባይን ውኃ በላይኛው ተፋሰስ በተለይም በኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች ላይ ማከማቸት ትነትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ እ.አ.አ በ1945 በሃሮልድ ሀርስት እና በሌሎችም ጥናቶች የተረጋገጠ ሳይንሳዊ እውነታ ነው።
ይህንን መርሕ ተከትላ ኢትዮጵያ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የሚይዘውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠናቅቃ ወደ ሥራ ማስገባቷ ያረጀውን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በተግባር ያፈረሰ እርምጃ ነው።
የግድቡ ልዩ ባሕርይ ፍሰትን የሚገድብ ሳይሆን ተርባይን በማንቀሳቀስ ውኃን በቀጥታ ወደ ታችኛው ተፋሰስ የሚለቅ መሆኑ በባለሙያዎች የተረጋገጠ ነው።
ያለፉት ጥቂት ዓመታት የዓባይን ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታ ከመሠረቱ የቀየሩ ታሪካዊ ክስተቶች የተመዘገቡባቸው ናቸው። ከግድቡ ስኬት ባሻገር እ.አ.አ ጥቅምት 13 ቀን 2024 የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ወደ ሕግነት ተቀይሮ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን በይፋ መመሥረቱ የውኃ ሀብት አስተዳደሩን ወደ ላቀ የባለብዙ ወገን ትብብር አሸጋግሮታል።
በአሁኑ ወቅት የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር እጅግ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ የምግብ፣ የውኃ እና የኃይል ፍላጎት ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል።
በመሆኑም የቆየው የአንድ ወገን የበላይነት መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ተጠቅማ ዜጎቿን ከድህነት የማውጣት መብቷ በተፈጥሮም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግጋት የተረጋገጠ ነው።
የዓባይ ጉዳይ ከእንግዲህ ጊዜ ባለፈበት የቅኝ ግዛት ውል ሊታሰር አይችልም። ብቸኛው እና አዋጩ መንገድ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ፍላጎት ያገናዘበ ፍትሐዊ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እና አዲሱን ትውልድ የሚመጥን የጋራ ትብብርን ማስፈን ነው።
ኢትዮጵያ ራሷ ለመልማት እንጂ ማንንም የመጉዳት ታሪክም ሆነ ፍላጎት እንደሌላት በተግባር አሳይታለች። ለዚህም ነው የተፋሰሱ ሀገራትን ትብብር ለማጠናከር ዛሬም በትጋት እየሠራች የምትገኘው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: