የአንድ ከተማ ዕውነተኛ እድገትና ሥልጣኔ የሚለካው በፎቆች መገንባት እና በጎዳናዎች ውበት ብቻ ሳይሆን፣ በችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎችን በማንሳት እና ክብራቸውን በመመለስ ጭምር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ከምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ትልቁ ሥራ በሰው ላይ የምንሰራው፣ በተለይም በሴቶች ላይ የምንሰራው ነው" በማለት ያስቀመጡት አቅጣጫ በመዲናችን አዲስ አበባ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል።
የዚህ ራዕይ ትልቁ ማሳያ ቀደም ሲል በጎዳና ሕይወት እና በከባድ ማኅበራዊ ቀውሶች ለእንግልት ተዳርገው የነበሩ እህቶቻችንን መታደግ መቻሉ ነው።
በተለይም "ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል" የሴቶችን ሰብዓዊ ክብር በመመለስ ረገድ አንጸባራቂ የለውጥ መንገድ ሆኗል።
ማዕከሉ ሴቶችን ከተረጂነት አስተሳሰብ በማላቀቅ ጥልቅ የስብዕና እና የሥነ-ልቦና ሕክምና ይሰጣል።
ከዚህም ባሻገር ዘመኑን የሚመጥን እና በገበያው ተፈላጊነት ያላቸውን የሙያ ክህሎቶች በማስጨበጥ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል።
ይህ የተቀናጀ አሠራር ሴቶቹ በራሳቸው እግር ቆመው አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ከማድረጉም በላይ፣ አምራች ኃይል በመሆን ለማኅበረሰቡ የምርታማነት መሰረት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
በዚህ አርዓያነት ባለው ተግባር እስካሁን 3 ሺህ 259 እህቶቻችን አስፈላጊውን የስብዕና እና የሙያ ሥልጠና አጠናቅቀው በክብር ወደ ሥራው ዓለም ተቀላቅለዋል።
ይህም ከጊዜያዊ የዕለት እርዳታ ሙሉ በሙሉ በመውጣት ዘላቂ በሆነ መንገድ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓቸዋል።
ሕይወታቸውን በብቃት ከመምራታቸውም ባሻገር በተመሳሳይ ማኅበራዊ ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ሕያው አርዓያ እና የተስፋ ምንጭ መሆን ችለዋል።
የሰው ተኮር ሥራዎች እውነተኛ ትርጉም የሚገለጸው ማኅበራዊ ፍትህ በሰፈነበት እና ለዘመናት የከረሙ ስብራቶች በተጠገኑበት በዚህ ተግባር ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: