ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የልህቀት ጉዞው ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካን የሲቪል አቪዬሽን ትምህርት ምህዳር በከፍተኛ ደረጃ የመቀየር እና በአህጉር ደረጃ ዘርፉን በዕውቀት የመምራት ስትራቴጂያዊ ሚናውን በብቃት እየተወጣ ነው።
በ1948 ዓ.ም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አካዳሚ ተመስርቶ ሥራ የጀመረው ይህ አንጋፋ ተቋም፣ ከተደረገው መዋቅራዊ ማሻሻያ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተሸጋግሮ ቀደም ሲል ይሰጣቸው ከነበሩት የሙያ እና የቴክኒክ የምሥክር ወረቀት ሥልጠናዎች ባሻገር ሰፊ የምርምር እና የከፍተኛ ትምህርት ዲግሪ መርሐ ግብሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ የብቃት ደረጃ ከኢፌዴሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን እና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን (ECAA) ሙሉ ዕውቅና ያገኘ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO)፣ ከአውሮፓ የአቪዬሽን ደኅንነት ኤጀንሲ (EASA) እና ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) የተሰጡት ዕውቅናዎች ተቋሙ በዓለም አቀፍ የጥራት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ አስችለውታል።
ዩኒቨርሲቲው ለ5 ዓመታት በሚሰጣቸው የኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ እና የአውሮፕላን ጥገና ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ስልጠናዎች ሰልጣኞች በዘመናዊ ቦይንግ 777፣ ቦይንግ 787፣ ኤርባስ ኤ350 እና ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ቀጥተኛ የተግባር ልምድ እንዲያገኙ ያደርጋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በሚገዛበት እና የበረራ መዳረሻዎቹን በሚያሰፋበት ፍጥነት ልክ የሰው ኃይል እጥረት እንዳይፈጠር ወሳኝ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል እንድትሆን በማድረግ ለአውሮፕላን ጥገና እና ለባለሙያዎች ሥልጠና ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማዳኑም በላይ፣ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን በማስተማር አዲስ የገቢ ምንጭ ፈጥሯል።
በአዲስ አበባ ቦሌ ካምፓስ ከሚገኙ ዘመናዊ የበረራ ሲሙሌተሮች በተጨማሪ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ እና በባሕር ዳር ቅርንጫፎችን በመክፈት ተደራሽነቱን ያሰፋው ተቋሙ፣ የተለያዩ ሀገራት ሠልጣኞችን ለመሳብ ባዘጋጃቸው ማበረታቻዎች የኢትዮጵያን አህጉራዊ ተወዳዳሪነትና መሪነት አጎልብቶታል።
እስከአሁን ከ52 ሀገራት የተውጣጡ ከ15 ሺህ በላይ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማፍራት የአፍሪካን የሲቪል አቪዬሽን ጥገኝነት የቀነሰው ይህ ግዙፍ ተቋም፣ ከዓለም አቀፉ የቦይንግ ኩባንያ እና ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሥራት አህጉራዊ አድማሱን አስፍቷል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 ግቦችን ለማሳካት እና በአፍሪካ ኅብረት የአንድ ወጥ የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ገበያ (SAATM) ኢኒሼቲቭን ለማሳካት የሚያስችለውን የሰው ኃይል የማቅረብ ብሔራዊ እና አህጉራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ በመወጣት፣ የአፍሪካን አቪዬሽን እና የኢትዮጵያን ልህቀት ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ በማሸጋገር ላይ ይገኛል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: