Search

የከተማ ውበት ከሰብዓዊ ክብር ጋር፦ የኮሪደር ልማት ያረጋገጠው ማኅበራዊ ፍትህ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 53

ለዘመናት ያረጀ ጣሪያ ሲያፈስስ፣ የተጣበበ ግድግዳ ሲደረመስ፣ እንዲሁም ዝናብ እና ብርድ የቤት ውስጥ ዘወትር እንግዳ ሲሆኑ ጉዳቱ አካላዊ መጠለያ በማጣት ብቻ አይወሰንም።

ይልቁንም የሰውን ልጅ የመኖር ተስፋ፣ በራስ የመተማመን ስሜት እና የማኅበራዊ ሕይወት ባለቤትነትን ቀስ በቀስ እየሸረሸረ የሚሄድ ሥነ-ልቦናዊ ስብራት ያደርሳል።

ይህ እውነት ከጥቂት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ያው የመሐል ከተማዋን የሚገልጽ ነበረ።

ቀደም ሲል በከተማዋ ለሰው ልጆች አኗኗር በማይመጥኑ አስቸጋሪ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ እና የሕይወት ብርሃን ፈንጥቆላቸው አዲስ ምዕራፍ ጀምረዋል።

በከተማዋ በስፋት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከቀላል የከተማ ውበት እና የቁሳቁስ ድጋፍ አልፎ የዜጎችን ሥነ-ልቦናዊ ክብር የመመለስ እና ማኅበራዊ ፍትህን የማረጋገጥ ራዕይ ሕያው ማሳያ ሆኗል።

በልማቱ ምክንያት ቀድሞ ለሰው ልጆች አኗኗር ከማይመጥን ስፍራቸው ለተነሱ ነዋሪዎች የተገነቡት አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ዘመናዊነትን የተላበሱ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው።

ከምንም በላይ ደግሞ ነዋሪዎቹ ቀድሞ የነበራቸው ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ እሴት እና አብሮነት እንዳይበጠስ በአንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጉ የልማቱን ሰው ተኮርነት ያጉላዋል።

በአዲሶቹ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች ውስጥ ነዋሪዎቹ ከእንግልት እንዲድኑ እንደ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ያሉ ወሳኝ ማኅበራዊ መሰረተ ልማቶች በአቅራቢያቸው ተሟልተውላቸዋል።

ከቤት አቅርቦቱ ጎን ለጎንም የነዋሪዎቹን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት ምቹ የሥራ ቦታዎች ተመቻችተውላቸው ቋሚ ገቢ እያመነጩ እንዲኖሩ ተደርጓል።

ቀደም ሲል በሚያቃጥል ፀሐይ እና በዝናብ በጎዳና ዳር ጉሊት እየሠሩ ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ የነበሩ እናቶች፣ ዛሬ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ በዘመናዊ የንግድ ሼዶች እና የማኅበረሰብ ገበያዎች ውስጥ ገብተው እየሠሩ ይገኛሉ።

ይህም የከተማዋን ገበያ ስፍራዎች ጽዳት እና ውበት ከመጠበቁም በላይ ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ዜጎችን ወደ አምራች እና ውጤታማ ነጋዴነት አሸጋግሯቸዋል።

የኮሪደር ልማቱ ዋና ዓላማ መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት የከተማን መልክ ማደስ ብቻ ሳይሆን፣ ከሰው ልጅ ደረጃ በታች የነበረን ሕይወት ወደ ተጠበቀ ሰብዓዊ ክብር እና ሁለንተናዊ ራስን መቻል ማሸጋገር መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል።

በሃና ምንዳሁን

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: