ዘመናትን የተሻገሩ የኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስብራቶች በአንድ ጀምበር ያልተፈጠሩ እንደመሆናቸው፤ የተከማቹ ቅሬታዎችንና ቁስሎችን በማከም መደላደል ለመፍጠርና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም ከፍተኛ ጊዜን፣ ትዕግስትንና የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ ረጅም ጉዞ ነው።
ሀገራችን ለዘመናት ሲፈታተኗት የቆዩ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በአፈሙዝ ሳይሆን በዜጎች ነፃ ውይይት ለመፍታት አልማ ያካሄደችውና በቅርቡ የተቋጨው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ትልቅ ስኬት ነው።
ሀገር የምትገነባው፣ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው እና ዴሞክራሲ የሚጸናው በዜጎች የጋራ መግባባት መሆኑን ያስመሰከረው ሀገራዊ ምክክር በታሪካችን በወርቃማ ቀለም የሚሰፍር ታሪካዊ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች በቀጥታ የተሳተፉበት ታሪካዊ ሂደት የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ መሠረታዊ አጀንዳዎች ተነስተው ሰፊ ምክረ-ሀሳቦች የተሰንዱበት ሆኗል።
ሂደቱ ከጥንት ጀምሮ ችግሮችን በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ ጠብመንጃ መወልወል ለለመደው የፖለቲካ ባህላችን መፍትሔው ንግግርና ውይይት ብቻ ነው የሚል ቁርጠኛና ታሪካዊ መልዕክት አስተላልፏል።
በሕዝቦችና በፖለቲካ ልሂቃን መካከል የነበሩ የሚያራርቁ ትርክቶችና ቅሬታዎች ወደ መድረክ መጥተው በግልጽ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ በጽኑ መሠረት ላይ ሆኖ ግጭትን በማውገዝና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትን መርህ በማድረግ የልዩነት ምንጭ የነበሩ ጉዳዮችን በማኅበራዊ ውል ተክቷቸዋል።
ይህ ስኬት ለዘላቂ ሰላም፣ ለሰላማዊ የችግር አፈታትና ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ የጣለ ከመሆኑም በላይ፣ ውስብስብ ችግሮች ባሉባቸው ሀገራት ምክክርን እንዴት በነፃነት ማካሄድ እንደሚቻል አዎንታዊ ተሞክሮ የሚሆን መሠረት ያስቀመጠ ነው።
ጥንት በዓድዋ፣ በዚህ ትውልድ ደግሞ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ለስኬት በማድረስ ታሪክ የሰራው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ግጭትንና አለመግባባትን በትዕግሥትና በጽናት ማሳለፉ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ድል ዋና መሠረት ሆኗል።
ይህ ታሪካዊ ምክክር በኢትዮጵያ ምድር የልዩነት ሳይሆን የአንድነት፣ የቂም ሳይሆን የፍቅርና የወንድማማችነት ምንጭ የሆነ አዲስ ባህል ነው።
የተሰበሩ ድልድዮችን በመጠገን፣ የጋራ ትርክትን በመፍጠር እና የባዕዳንን የጣልቃ ገብነት በር በመዝጋት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠው ይህ የሰላምና የእርቅ መንፈስ፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ ተቀምጠው በሀገራቸው ጉዳይ በመምከር ከኃይል አዙሪት ወጥተው በሰለጠነ መንገድ መተማመን እንደሚችሉ ያበሰረ ታላቅ ድል ነው።
አሁን ላይ ዜጎች በነፃነት ተወያይተው የዘረጉትን ይህን ሰላማዊ መንገድ በቅብብሎሽ ማስቀጠል፣ ወንድማማችነታችንን ይበልጥ በማጠናከር የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ማድረግና ዴሞክራሲን ማጽናት የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: