የኢትዮጵያ እና ታይላንድን ሁለንተናዊ ትብብር እና አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና በይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ የሚገኙት የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉዋንግኬትክየው ናቸው።
የታይላንዱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በስምምነቱ ፊርማ ወቅት ባደረጉት ንግግር ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት አጋርነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ታይላንድ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጎልበት ተመሳሳይ ራዕይ ሰንቀው በጋራ በመጓዝ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የተደረሰው ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማስተሳሰር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው በአጽንኦት ገልጸዋል።
ከሁለትዮሽ ስምምነቱ ባለፈ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ጉብኝት ሌላም ትልቅ አህጉራዊ ክንውን አስተናግዷል። ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው "የታይላንድ-አፍሪካ ኢኒሼቲቭ"ን በይፋ አስጀምረዋል።
የሥራ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ እና ታይላንድ መካከል እያደገ የመጣውን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑ ተመላክቷል።
በወንድማገኝ ኃይሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: