በአንድ ሀገር የዕድገት ጉዞ ውስጥ ትልቁ ካፒታል የነገን ራዕይ ሰንቀው የሚነሡ ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ናቸው።
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ሲገለጽም፣ ኢትዮጵያ መፃኢ ጊዜዋን በልበ ሙሉነት ልታስረክባቸው የምትችላቸውን ብሩህ ተስፋዎች ተመልክታለች።
ከእነዚህ ሀገር አኩሪ ኮከቦች መካከል ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሀድያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሊች ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ሮቤል ጌታቸው አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
በሀገር አቀፍ ፈተናው ከፍተኛው ውጤት 591.6 ሆኖ በተመዘገበበት በዚህ ዓመት፣ ተማሪ ሮቤል ከ600 ውስጥ 590.08 ውጤት በማስመዝገብ በሀገር ደረጃ ሁለተኛውን ከፍተኛ ደረጃ ተቆናጥጧል።
ይህ አኩሪ ስኬት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን በዓላማ፣ በጠንካራ የጥናት ስልት እና በማያወላውል ትኩረት የተገነባ፣ የለፋበትን እና የደከመበትን እልህ አስጨራሽ ጉዞ የሚያሳይ የድካም ፍሬ ነው።
የሮቤል ስኬት ከኋላው ብዙ የሚነገሩ ትምህርት ሰጪ ታሪኮች አሉት። ይህም የንባብ ጊዜውን በከፍተኛ ትኩረት ማሳለፍ፣ ማስታወሻ የመያዝ እና በርካታ ጥያቄዎችን የመሥራት የዳበረ ልምድ ያለው መሆኑ ነው።
ሮቤል ለ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የተዘጋጀበት መንገድ ውጤታማ እንዳደረገው ይናገራል። ከምንም በላይ ደግሞ ለደረሰበት ከፍታ የወላጆቹ ዐሻራ ጎልቶ ይታያል። እናት እና አባቱ መምህራን መሆናቸውን እና እነሱ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ መሆናቸው እርሱም ሙሉ ትኩረቱን ትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ አስችሎታል።
የምናልመው ነገር ትልቅ ከሆነ የሚመጣው ውጤትም በተመሳሳይ ከፍተኛ እንደሚሆን ጽኑ እምነት አለው፤ ይህንንም በተግባር አሳይቷል።
በዚህ አስደናቂ ውጤቱ ምክንያት የክልሉ መንግሥት እና የትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማቸው በመግለጽ፣ ልዩ የማበረታቻ ሽልማት አበርክተውለታል።
ሮቤል ጌታቸው፣ ቀጣይ ጉዞው ሰማየ ሰማያትን ሰንጥቆ መብረር ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በልቡ ያሳደገውን የአውሮፕላን አብራሪነት (ፓይለት) ሕልሙን እውን በማድረግ፣ በአቪዬሽኑ ዘርፍ ጥሩ ቦታ የመድረስ ጽኑ ራዕይ እንዳለው አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል።
በእርግጥም የሮቤል ታሪክ የውጤት ብቻ ሳይሆን፣ የትልቅ ሕልም፣ የዓላማ ጽናት፣ እና የትኩረት ማሳያ ነው። እሱ ለትውልዱ አብነት፣ ለሀገሩም ሌላኛው ብሩህ ተስፋ ነው!
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: