የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ ሰላምን፣ መከባበርን እና አንድነትን ለማስፈን ላበረከተው አስተዋጽኦ የዓለም አቀፍ የሰላም ዕውቅና ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ይፋ ሆነ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተመሠረተበትን 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ በደመቀ ሁኔታ አክብሯል።
በመድረኩ የዓለም የሃይማኖት እና የባህላዊ ሰላም ግንባታ ኔትዎርክ (Network for Religious and Traditional Peacemakers) ተወካይ ኢትዮጵያ ለሰላም ግንባታ የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴርን በማቋቋም ለዓለም አርአያ የሚሆን ተግባር ማከናወኗን የጠቀሱት ተወካዩ፣ ይህም ሀገራችን ለሰላም የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። ወቅቱ ዓለም ሰላምን አጥብቃ የምትሻበት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የነጃሺ ምድር እና የመጀመሪያው የእስልምና ስደት (ሒጅራ) በክብር የተስተናገደባት ሀገር መሆኗን አስታውሰው፣ ሀገራችን ለዘመናት የዘለቀ የማኅበራዊ ትሥሥር፣ የትዕግሥት እና የአብሮነት ተምሳሌት መሆኗንም ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የዓለም የሃይማኖት እና የባህላዊ ሰላም ግንባታ ኔትዎርክ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ላከናወናቸው ውጤታማ የሰላም ሥራዎች ይህንን የክብር ሽልማት ለመስጠት መወሰኑን ይፋ አድርገዋል። ሽልማቱም ነገ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ከ56 ሀገራት የተወከሉ የ120 ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በሚካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በይፋ እንደሚበረከት ነው የጠቆሙት።
“ከመቶ በላይ አባላት የሚሳተፉበትን ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ በሰላሟ ምድር፣ በማኅበራዊ ትሥሥር እና በመግባባት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያ በማድረጋችን ታላቅ ክብር ይሰማናል” ብለዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ ኔትዎርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን ሪፖርት መሠረት የተቋቋመ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ ለሰላም ግንባታ እና ለግጭት አወጋገድ የሃይማኖት አባቶች እና የባህላዊ መሪዎች ያላቸውን ጉልህ ሚና ለማጎልበት በንቃት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገር ሰላም እና አብሮነት ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑ በመድረኩ ተነሥቷል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: