እግር ኳስ ውድ ልጇን እየተሰናበተች ነው። የነገሩ መነሻ የ23ኛው ዓለም ዋንጫ ሽንፈት፣ ሕይወቱን ያጎደለው የወላጅ አባቱ ሆርሄ ሜሲ ሕልፈት ወይስ ዕድሜ? ከተባለ መልሱ ሁሉንም የሚል ይሆናል።
በእርግጥ እርሱ ለእግር ኳስ ሁሉንም ነገር ሰጥቷል፤ የሰሰተው አንዳች ነገር የለም የሚለው ለክርክር የሚቀርብ ላይሆን ይችላል።
ሊዮኔል ሜሲ ከላ ማሲያ ተነሥቶ የካታላኑ ኃያል ክለብ ኩራት ብቻ ሆኖ አልቀረም፣ ትዝታው በፈረንሳይ እና አሜሪካ ክለቦች ባሳለፋቸው ዘመናት ብቻ የሚዘጋም አይደለም።
ለ‛አልበሰልስቴዎች’ ከዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና የእግር ኳስም የምድርም ስንብት በኋላ ከድል ጋር ያገናኛቸው፣ ከተስፋ መቁረጥ ዳርቻ የመለሳቸው ውድ ልጃቸው ነው እና ይህን የስንብት ዜና በዋዛ የሚያልፉት አይሆንም።
በ2014 ከዓለም ሻምፒዮንነት ደጃፍ ላይ ቆመው ጀርመን ስታስቀራቸው፤ በ2007፣ 2015 እና 2016 በአህጉራዊው የኮፓ አሜሪካ ውድድር ፍጻሜዎች የዋንጫውን አንድ እጀታ እየጨበጡ አሳልፈው ሲሰጡ መንገዱ ፈተና ገጥሞታል። ይህን ተከትሎ የተሰነዘሩ ትችቶችን ጫንቃው የማይችለው ሆኖ ሲሰማው ገና በ29 ዓመቱ “ጉዞው አብቅቷል” በማለት ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን መሰናበቱን እስከማወጅ ደርሶ ነበር።
በዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና ጭምር “የመሪነት ስብእናን ያልተላበሰ” ተብሎ ሲተች በቃኝ ቢልም፣ የወቅቱ የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት ማውሪዚዮ ማክሪን ጨምሮ በርካቶች ያሰሙትን የ“አስብበት” ተማጽኖ ሰምቶ፣ ቡድኑን ያላንተ ማሰብ እንዴት ይቻላል ለሚለው ውትወታ እጅ ሰጥቶ ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ዳግም ለመጫወት ወሰነ። የዓለም እግር ኳስም ሌላ ውብ ዐሥር ዓመታት ተጨመረለት።
የኮፓ አሜሪካ እና የምድራችን ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ዓለም ዋንጫ የሻምፒዮንነት ጥያቄዎችም በእነዚያ ዐሥር ዓመታት ተመለሱ። በመውጣት እና መውረድ ውስጥም “ሀገሬን እና ይህን መለያ በጣም ነው የምወዳቸው” እያለ እግር ኳስ ያሉትን ለእርሱ ግን ጎድለውት የነበሩትን ክብሮች ሁሉ ተራ በተራ አሳካ። ለአርጀንቲናም አለኝታ ሆነ።
ሊዮኔል ሜሲ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ሁለት ዐሥርት ዓመታት በተሻገረ ቆይታው በ207 ጨዋታዎች 125 ግቦችን አስቆጥሯል፣ 11 ጊዜ ሐትሪክ ሠርቷል። በ6 ዓለም ዋንጫዎች 34 ጨዋታዎችን በማድረግም የመጀመሪያው ተጫዋች ተሰኝቷል።
አሁን አዳዲስ ወጣት ኮከቦች እርሱ ባለፈበት የስኬት መንገድ ያልፉ ዘንድ አዲሱን መንገድ መጀመሩን አስታውቋል። “ስሰናበት ፍጹም ሰላም እየተሰማኝ፣ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላቀው መንገዴም እየኮራሁ ነው” ብሏል።
ከዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ሁለት ቀን በኋላ እንደጻፈው ሆኖም በወላጅ አባቱ ኅልፈት ምክንያት እንዳዘገየው በገለጸው የስንብት መልዕክት፣ ውሳኔው ከዚያም አስቀድሞ የደረሰበት እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
ከአባቱ ሕልፈት በኋላ የተናገረው “ከዚህ በኋላ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ብዙ የምቆይ አይመስለኝም” ሲል የተናገረው ሐሳብ አንደኛው ክፍል አሁን ተዘግቷል። ዘመናዊ እግር ኳስ አንድ ጌጡን እየተነጠቀ ስለመሆኑም ይህ ሌላኛው ምልክት ሆኗል።
“የቀረ ጊዜ የለም፤ የተለያየ መልክ ያላቸው ምዕራፎችም ወደ ፍጻሜያቸው እየቀረቡ ነው” የሚለው የሊዮኔል ሜሲ የብሔራዊ ቡድን ስንብት አንኳር ነጥብ ነው።
በነዚያ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ባለፉ በኀዘን እና ደስታ፣ በማግኘት እና ማጣት፣ በድል እና ሽንፈት ብሎም በደስታ እና እንባ የታጀቡ ምዕራፎች ውስጥ ትዝታ አለ። ውብ የእግር ኳስ ትዝታ፣ በሰው እና በዘመን መሄድ የማይደበዝዝ ትዝታ!
በእድሪስ አሕመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: