የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በርካታ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ የሆኑ ተማሪዎችን አስተዋውቆናል።
ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል የአትላስ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት መንትዮቹ ወንድማማቾች፣ አቤንዘር ጎሳዬ እና ኒቆዲሞስ ጎሳዬ አስደናቂ ስኬት ይጠቀሳል። የእነዚህ መንትዮች ውጤት ብዙዎችን ያስደመመ እና ለሌሎች ተማሪዎች ትልቅ ትምህርት የሰነቀ ነው።
የእነዚህ ሁለት ወጣቶች ጉዞ፣ በውጤት የታጀበ ብቻ ሳይሆን በጽናት እና በትጋት የተሞላ ነው። በሀገር አቀፍ ፈተናው አቤንዘር ጎሳዬ 547.41 ሲያስመዘግብ፣ መንትያ ወንድሙ ኒቆዲሞስ ጎሳዬ ደግሞ 529.92 አምጥቶ በከፍተኛ ውጤት አጠናቅቀዋል።
የሁለቱ ወጣቶች የስኬት ምሥጢር እና የሕይወት ተሞክሮ ለበርካቶች ማነቃቂያ ነው። የአቤንዘር እና የኒቆዲሞስ የትምህርት ጉዞ የጀመረው ገና በልጅነታቸው በሽመልስ ሀብቴ፣ ሆሊ ስፒሪት እና ዴንማርክስ ትምህርት ቤቶች ነበር።
በኋላም ወደ አትላስ ትምህርት ቤት በማቅናት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ዘልቀዋል። በቆይታቸውም ሁልጊዜም በክፍላቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ከመሆን ዝቅ ብለው አያውቁም።
በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት እነዚህ መንትያ ወጣቶች፣ በሁለተኛ ደረጃ ቆይታቸውም በአትላስ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት የነጻ ትምህርት ዕድል በማግኘት ወላጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ክፍያ ማሳረፍ ችለዋል።
ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በሒሳብ ውድድሮች እስከ ሀገር አቀፍ ደረጃ በመሳተፍ የሜዳሊያ እና የሰርተፍኬት ተሸላሚ መሆን ችለም።
በመንትዮች መካከል ብዙ ጊዜ ፉክክር ሳይሆን ትብብር ትልቅ ቦታ አለው። አቤንዘር ሲሰለች ኒቆዲሞስ ያበረታታዋል፤ ኒቆዲሞስን የከበደው ጥያቄ ሲኖር አቤንዘር ይረዳዋል። አንዱ ቀደም ብሎ ያጠናውን ለሌላኛው በማካፈል እና አብሮ በመሥራት፣ አንዱ የአንዱ ምርኩዝ በመሆን ለታላቅ ውጤት በቅተዋል።
ይህ የመረዳዳት ባህላቸው በቤት ውስጥ ብቻ ሳይወሰን፣ በትምህርት ቤታቸውም በውጤታቸው ዝቅ ያሉ ተማሪዎችን በመርዳት እና በማስጠናት ይታወቃሉ። የእነሱ ትምህርት ቤት (አትላስ) በ2018 ዓ.ም ተማሪዎቹን መቶ በመቶ ማሳለፉም የእነዚህ ወጣቶች የቡድን ሥራ ውጤት ጭምር ነው።
እነዚህ ወጣቶች ለራሳቸው ውጤት ብቻ የሚጨነቁ አይደሉም። "ከእኛ ለእኛ" የተሰኘ የቴሌግራም ቻናል በመክፈት፣ ለሌሎች ተማሪዎች የጥናት ግብዓቶችን፣ የፈተና ጥቆማዎችን እና የስኮላርሺፕ መረጃዎችን በነጻ ያካፍላሉ። ይህም ዕውቀትን ለሌሎች ማካፈል የውስጥ እርካታ እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ያሳያል።
ወደፊት በኮምፒውተር ሳይንስ፣ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፎች የመማር ትልቅ ሕልም አላቸው። ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ የበለጸገች እና በሰላም የምትመራ ሀገር ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያልማሉ።
መንትዮቹ ለወጣት ተማሪዎች ማንኛውንም ሥራ ከመጀመር በፊት ፈጣሪን ማስቀደም፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ልምምድ ማድረግ፤ ዕውቀትን ለሌሎች በማካፈል የራስን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የአቤንዘር እና የኒቆዲሞስ ስኬት፣ "በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማንኛውም ስኬት ተምሳሌት ነው" የሚለውን እውነት ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች በተግባር ያስመሰከረ የስኬት ታሪክ ነው።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: