በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት፣ የአውሮፓ የፖለቲካ አደባባዮች የዓለምን ካርታ እንደገና ለመቅረጽ በተሰበሰቡ ኃያላን ሀገራት ተጨናንቀው ነበር።
በተለይም በለንደን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በፓሪሱ የሰላም ጉባኤ ላይ፣ የጣሊያንን የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች ዕጣ ፈንታ የመወሰኑ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቀረበ።
በእነዚህ መድረኮች ላይ የዓለም ታላላቆቹ እነ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሶቭየት ኅብረት የየራሳቸውን የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሻኮቱ፣ በዚያ ግዙፍ የዲፕሎማሲ ማዕበል ውስጥ የኢትዮጵያን የዘመናት ታሪክ፣ ክብር እና የባሕር በር የሕልውና ጥያቄ ተሸክመው ለብቻቸው የቆሙት ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ነበሩ።
«የአክሊሉ ማስታወሻ» በተሰኘው መድብል በግልጽ እንደተጻፈው፣ ይህ ጉዞ በቀላል ቋንቋ ዲፕሎማሲ ብቻ ተብሎ የሚገለጽ አልነበረም፤ የብዕር፣ የወረቀት፣ የሕግ እና የሞት ሽረት ትግል እንጂ።
ኢትዮጵያን ከባሕር በሯ ለማገናኘት ለ700 ሰዓታት በአውሮፕላን በርረዋል፤ ከሺህ በላይ ገጾች ያሉት የጽሑፍ ሰነድ አዘጋጅተዋል፤ ወጥተዋል ወርደዋል። በመጨረሻም በጽኑ ታምመው በሆስፒታል አልጋ ላይ ቢወድቁም፣ ከአልጋቸው ተነሥተው ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል።
በለንደኑ ጉባኤ፣ የተሸናፊዋ ጣሊያን ልዑካን ሳይቀሩ ኤርትራን በሞግዚትነት ለማስተዳደር ሲከራከሩ፣ ዲፕሎማት እና ዐርበኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ያቀረቡት የመልስ ምት የዲፕሎማሲውን ዓለም ያስደነገጠ ነበር።
እንግሊዞች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ አድርገው ለማስቀረት የሚያስችላቸውን የረቀቀ ሴራ ሲያቀርቡ፣ አክሊሉ እያንዳንዱን የሕግ እና የታሪክ ሰነድ እያገላበጡ፣ በማያወላውል አመክንዮ የኃያላኑን መከራከሪያ መሬት ላይ ያፈርጡት ገቡ።
ቀኖቹ በስብሰባ አዳራሽ በሚደረጉ እልህ አስጨራሽ ክርክሮች ሲጠናቀቁ፣ ሌሊቶቹ ደግሞ ለቀጣዩ ቀን የሚቀርቡ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት፣ በማንበብ፣ በመጻፍ እና ሌሎች የልዑካን አባላትን በማሳመን ያልፉ ነበር።
ከለንደን ወደ ፓሪስ የሰላም ጉባኤ፣ ከዚያም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የተደረገው የትግል ሽግግር እጅግ አድካሚ፣ የሚያዝል እና ጤናን ጭምር የሚያናጋ ነበር።
ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ የሀገራቸው ጉዳይ እንቅልፍ ነሥቷቸው፣ ምግብ እንኳን መመገብ ዘንግተው፣ ሌሊት እና ቀን ከአንዱ ኮሪደር ወደ ሌላው፣ ከአንዱ ሀገር ተወካይ ወደ ሌላው ሲንከራተቱ ሰውነታቸው ዝሎ ነበር።
አንዲትን ጥንታዊት ሀገር ከነ ክብሯ ወደብ አልባ አድርጎ ለማስቀረት የተጠነሰሰው ዓለም አቀፍ ሴራ በአዕምሯቸው ላይ የፈጠረው ጫና፣ እንዲሁም በየመድረኩ የሚያደርጉት ንዴት እና ቁጭት የተቀላቀለበት ሙግት በአካላዊ ጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከተለ።
ቀስ በቀስ የድካም እና የጭንቀት ብዛት አቅማቸውን አዳከመው፤ ሰውነታቸውም በእጅጉ ተጎዳ። በመጨረሻም ሐኪሞች ሁኔታቸው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አረጋግጠው፣ ማንኛውንም እንቅስቃሴ አቁመው በሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እንዲከታተሉ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጡ።
አክሊሉ ግን ሆስፒታል አልጋ ላይ ወድቀውም፣ ነፍሳቸው የምትቃትተው ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር እና ስለ ኤርትራ ወደ እናት ሀገሯ የመመለስ ጉዳይ ነበር። ኃያላኑ ሀገራት የኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት በሚዶልቱበት በዚያ ወሳኝ ሰዓት፣ እርሳቸው በአልጋ ላይ መዋላቸው እጅግ አብግኗቸው ነበር።
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በሚወሰንበት እና የድምፅ አሰጣጡ ሒደት ሊካሄድ በተቃረበበት ሰዓት፣ አክሊሉ የሕክምና ባለሙያዎችን ትዕዛዝ ጥሰው፣ በጠና የታመመ አካላቸውን እየጎተቱ፣ ከልብ በሆነ ቆራጥነት ወደ ጉባኤው አዳራሽ ተመለሱ።
በዚያ ታሪካዊ መድረክ ላይ የተገኙት የዓለም ዲፕሎማቶች፣ በሕመም የሚንገዳገደውን ነገር ግን በማይበገር ቁርጠኝነት ወደ ማይክሮፎኑ የተጠጋውን ይህንን ኢትዮጵያዊ ዐርበኛ በከፍተኛ ዝምታ ተመለከቱት።
ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በዚያች ታሪካዊ መድረክ ትንፋሻቸውን ሰብስበው፣ የዓለምን ሕሊና የሞገተውን ያንን ታሪካዊ ንግግራቸውን አሰሙ።
በተለይም የባሕር በር ባለቤትነትን በተመለከተ፣ የኢትዮጵያን ሕልውና እና ፍትሕን አዋህደው ያቀረቡት ንግግር በማስታወሻቸው ላይ እንዲህ በሚል ቃል በቃል ተቀምጧል፦
"ኢትዮጵያ በፋሺስት ወረራ የመጀመሪያዋ ሰለባ ሆና እና ከፍተኛ ዋጋ ከፍላ ሳለች፣ ዛሬ በዚህ የሰላም ጉባኤ ላይ የፍትሕ ያለህ እያለች ትገኛለች። የኤርትራ ወደ እናት ሀገሯ መመለስ እና የባሕር በሮቿ ጉዳይ ለእኛ የድንበር ማስፋፋት ወይም የፖለቲካ ቅንጦት ጥያቄ አይደለም፤ የሕይወት እና የሞት፣ እንዲሁም የሕልውና ጉዳይ እንጂ። ለስድሳ ዓመታት በቅኝ ገዥዎች ተከብባ ትንፋሽ ያጠረባትን ሀገር፣ ዛሬም የባሕር በር ነፍጎ እንደታፈነች እንድትቀር መፍረድ በታሪክ ፊት ተጠያቂነትን የሚያስከትል ታላቅ ግፍ ነው። ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር፣ ልክ ያለ ሳንባ እንደመኖር ይቆጠርባታል። ፍትሕ ካለ፣ የዓለም ሕሊና የሚሠራ ከሆነ፣ ይህ የተከበረ ጉባኤ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነት መብት ሊያረጋግጥ ግድ ይላል!"
በዚህ ሙሉ ንግግር በእያንዳንዱ ቃል ውስጥ የዘመናት የኢትዮጵያውያን ቁጭት፣ የነጻነት ጥማት እና የባለቤትነት ስሜት እንደተዳፈነ እሳት ይንቀለቀል ነበር።
ያ በሕመም የተጎዳ ድምፅ፣ የኃያላኑን ሀገራት ልብ የሰበረ፣ የፍትሕ ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያጋድል ያደረገ ታላቅ የሞራል ኃይል ነበረው።
የጠነሰሱት ሴራ ሁሉ በዚህ ብርቱ ዐርበኛ ጽናት፣ ዕውቀት እና መሥዋዕትነት መክኖ ቀረ። በመጨረሻም የዲፕሎማሲው ትግል ፍሬ አፈራ፤ ኢትዮጵያም በምጽዋ እና አሰብ ወደቦች በኩል የባሕር በር ባለቤት ሆና ዳግም በዓለም ካርታ ላይ ደመቀች።
ይህ እጅግ አስደናቂ የሆነ የታላቁ ዲፕሎማት እና ዐርበኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ታሪክ፣ ዛሬ ላይ ላሉት እና ወደፊት ለሚመጡት ትውልዶች የሚያስተላልፈው እጅግ ጥልቅ የሆነ መልዕክት አለው።
ዛሬም ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ፣ በኢኮኖሚ አቅሟ እና በቀጣናዊ ተጽዕኖዋ እያደገች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ እንደገና የዘመናችን ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ይህ ትውልድ ከአክሊሉ ትግል ሊማር የሚገባው ትልቁ ነገር፣ የሀገርን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ጉዞ አልጋ በአልጋ አለመሆኑን ነው።
እንደ አክሊሉ በውጭ ኃይሎች ጫና ሳይንበረከኩ፣ ቀን እና ሌሊት ያለመታከት በማንበብ፣ በመመራመር፣ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በማያወላውል አመክንዮ ለመከራከር መዘጋጀትን ይጠይቃል።
የዛሬው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ፣ የትናንቱን የአክሊሉን የማይነጥፍ ቁጭት፣ የባለቤትነት መንፈስ እና ዲፕሎማሲያዊ ዐርበኝነት በድጋሚ የሚሻ ነው።
በጠና ታሞ፣ አልጋ ላይ ወድቆ፣ የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ ሀገርን ያህል ክቡር ነገር የባሕር በር ባለቤት ያደረገው ያ ትውልድ ከቻለ፣ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በተሻለ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ዓለም አቀፍ ትሥሥር ታጥቆ ይህንን የቁጭት እና የሕልውና ጉዞ በስኬት ዳር ማድረስ እንደሚችል አያጠራጥርም።
የባሕር በር ባለቤት የመሆን ሕልም በጽናት፣ በጥበብ እና በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ወደ እውንነት የሚቀየር፣ ይህ ትውልድ ዳግም አሸናፊነቱን የሚያረጋግጥበት የክብር ታሪክ ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: