የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች አሸናፊ ግርማ በሆነው እና በካናዳ በሚገኘው አካዳሚ ወስጥ የሚሰለጥኑ ታዳጊዎች እና ቤተሰቦቻቸው በባንካችን ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው ጉብኝት እና ውይይት አካሂደዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በባንካችን የማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ተስፋ ተክሌ ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች የቀረበ ሲሆን፣ የባንኩ የሪቴል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ አለሙ ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ባንኩ ስለሚሰጣቸው የዳያስፖራ አገልግሎቶች ገለፃ አድርገዋል።
አቶ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመደበኛው እና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማቅረቡን ጠቅሰው፣ ይህንኑ ይበልጥ ለማሳለጥ "የዳያስፖራ ዴስክ" በማቋቋም ልዩ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ጉብኝቱ የባንኩን ሀገራዊ አስተዋጽኦ በውጭ ሀገራት ለሚገኘው አዲሱ ትውልድ እና ቤተሰብ ለማስረዳት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ጨምሮ በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ፍጹም፣ ዳያስፖራው በሀገሩ ሀብት እንዲያፈራ እና የውጭ ምንዛሪን በቀላሉ እንዲልክ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩንም አስረድተዋል።
"ትውልድን በእግር ኳስ እናስተሳስር" የተሰኘው ፕሮጀክት መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አሰልጣኝ አሸናፊ ግርማ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ታዳጊዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሀገር ቤት በማምጣት ሀገራቸውን እንዲያውቁና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በስፖርቱ ዘርፍ ተቀራርቦ ለመሥራት እድሉን በማግኘታቸውም የተሰማቸውን ደስታ ማጋራታቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: