Search

የትብብር ጌጥ፣ የዜጎች ሕይወት መታደስ እና የሀገራዊ አንድነት መገለጫ፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

ማክሰኞ ነሐሴ 26, 2018 126

በሐረር ከተማ የሚኖሩት የአምስት ልጆች እናት ወይዘሮ አይሻ ኢብራሂም፣ በጉልበት ሥራ እየደከሙ ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩ ብርቱ ሴት ናቸው።

በመኖሪያ ቤት እጦት ምክንያት ለከፍተኛ የመጠለያ ችግር ተጋልጠው የነበሩት ወይዘሮ አይሻ፣ ዛሬ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነባላቸውን አዲስ ቤት ተረክበው አዲሱን ዘመን በሙሉ ደስታ ለመቀበል ተዘጋጅተዋል።

የወይዘሮ አይሻ ታሪክ በሐረሪ ክልል እየተከናወነ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዜጎች ሕይወት ላይ የፈጠረውን ሕይወት ቀያሪ በጎ ተፅዕኖ የሚያሳይ ናሙና ነው።

እንደ እርሳቸው ሁሉ ለዓመታት በመጠለያ እጦት እና በኢኮኖሚ መዳከም ውስጥ የነበሩ በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖች፣ ዛሬ የዚህ ቅዱስ ተግባር ቀጥተኛ ተጠቃሚ በመሆን የክብር እና የደህንነት ባለቤት መሆን ችለዋል።

ይህ በወይዘሮ አይሻ እና በሌሎች ወገኖች ቤት ውስጥ የበራው የደስታ ብርሃን፣ በክልሉ በየዓመቱ እየጎለበተ እና ሥር እየሰደደ የመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገኘው በረከት ነው።

ንቅናቄው ማኅበረሰባዊ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ባህልን ያሳደገ እንዲሁም የዜጎች የእርስ በርስ መደጋገፍ እና የወገንን እንባ የማበስ አቅም በተግባር የታየበት ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው ክረምትም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በላቀ ተነሳሽነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም ለአቅመ ደካሞች እየተገነቡ ያሉ መኖሪያ ቤቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

በሐረሪ ክልል 14 የተለያዩ የልማት ዘርፎች 47 ሺህ በላይ ዜጎችን በማሳተፍ የተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

አገልግሎቱ የሀገር ልጆች ያለ ምንም ክፍያ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ለሀገር ግንባታ እንዲያበረክቱ በማድረግ የነቃ የዜግነት ሚናን የሚቀርጽ ወሳኝ ንቅናቄ ነው።

በጎ ፈቃደኝነት በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር ከማጠናከሩ በተጓዳኝ፣ እንደ ወይዘሮ አይሻ ያሉ ዜጎችን ከጥገኝነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግር የማኅበራዊ ዋስትና መሠረት መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

በጋራ ጥረት የሀገርን ሸክም ለማቃለል፣ የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቀነስ እና የሀገርን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ዕድል ይፈጥራል።

ከወይዘሮ አይሻ ኢብራሂም አዲስ መጠለያ በስተጀርባ ያለው ታላቅ እውነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሀገር አንድነት እና የወንድማማችነት ማስተሳሰሪያ ገመድ መሆኑ ነው።

ይህ የደግነት እና የትብብር አሻራ አሁን ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ባህል እየሆነ የመጣ ዘላቂ ሀገራዊ እሴት ነው።

በቴዎድሮስ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: