Search

"ማኅበራዊ ሚዲያ የጥፋት መሣሪያ እንዳይሆን መመከት የሁላችንም የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል" — ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

ማክሰኞ ነሐሴ 26, 2018 112

 የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎችን ከማቀራረብ ይልቅ ልዩነትን በመዝራት የጥፋት መሣሪያ እንዳይሆን መመከት የሁሉንም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ገለጹ።

ዋና ጸሐፊው እንዳመለከቱት ማኅበራዊ ሚዲያ መጀመሪያውኑ ለመረጃ ልውውጥ፣ ለዕውቀት ማጋሪያ እና ሰዎችን ይበልጥ ለማቀራረብ ሊውል የሚገባው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ መልካም ዓላማው ተዛብቶ "ልዩነትን በማስፋት ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ እኩይ የጥፋት መሣሪያ" እየሆነ መጥቷል።

በመካከላችን አብሮነትን የማይሹ እና ብዝኃነትን ለማደብዘዝ ሌት ተቀን የሚሠሩ አካላት መኖራቸውን የጠቆሙት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፤ ይህንን አፍራሽ እንቅስቃሴ ከምንጩ ለማስቀረት ዳር ቆሞ መመልከት እንደማይገባ አሳስበዋል።

ጉዳዩን ለመንግሥት ወይም ለጥቂቶች ብቻ ሳይተው እያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት ሥራው አድርጎ ሊታገለው እንደሚገባ ተናግረዋል።

አክለውም፣ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን የማኅበራዊ ሚዲያን አሉታዊ ተፅዕኖ በመመከት ረገድ የሰላም ዘርን እንዲዘሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በተለይም የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን መንፈሳዊ ተሰሚነት በመጠቀም፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ለጥላቻ ሳይሆን ለፍቅር፣ ለይቅርታ እና ለሀገራዊ አንድነት እንዲውል ትውልዱን በግንባር ቀደምትነት ማስተማርና መምራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: