የባሕር በር ለኢትዮጵያ የዛሬ የኢኮኖሚ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የነገ ትውልድ ዕድልና የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው።
የዓለም ንግድ ከባሕር መስመሮች ጋር በጥብቅ በተሳሰረበት ዘመን፣ ወደብ ማግኘት ማለት የንግድ በር ብቻ መክፈት ሳይሆን የሀገርን ኢኮኖሚ አቅም፣ ተወዳዳሪነትና ቀጣናዊ ተሳትፎ ማሳደግ ማለት ነው።
ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ፣ በምርት አቅሟ እና በማደግ ላይ ባለው ኢኮኖሚዋ ለዓለም ገበያ የምታቀርበውን ምርት ለማሳደግ ተስማሚ የንግድና የሎጂስቲክስ አውታር ያስፈልጋታል።
በዚህ ረገድ የባሕር በር ጉዳይ ከወደብ በላይ የሚሻገር ትርጉም አለው። ከአርሶ አደሩ ምርት ጀምሮ እስከ ፋብሪካ ግብአት፣ ከኢንዱስትሪ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚዘልቅ የእሴት ሰንሰለት እንዲጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂያዊ አቅም ነው።
በተለይም የወደብ አማራጮችን ማብዛት እና የባሕር ንግድ መስመሮችን ማስፋት የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ የበለጠ ተለዋዋጭና ተወዳዳሪ ሊያደርገው ይችላል።
የሎጂስቲክስ ወጪ መቀነስ፣ የምርት ማጓጓዣ ጊዜን ማሳጠር፣ የወጪ ንግድን ማሳደግ እና የገቢ ምርቶችን በተሻለ ሁኔታ ማስገባት በቀጥታ በሃገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚታይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል።
የአሁኑ ትውልድ ከሚጠበቅበት ትልቁ ኃላፊነት አንዱ ሀገራዊ ጥቅምን ከአጭር ጊዜ ፍላጎት በላይ በማየት ለመጪው ትውልድ ዘላቂ መሠረት መጣል ነው። የባሕር በር ጉዳይም በዚህ የትውልድ ኃላፊነት መነጽር መታየት አለበት።
ዛሬ የምንገነባው የመንገድና የባቡር መሠረተ ልማት፣ የሎጂስቲክስ አቅም፣ የንግድ ትስስር እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነገ ላይ የሚያገለግል የትውልድ ካፒታል ነው።
ይህም የባሕር በርን እንደ አንድ የወደብ ጉዳይ ሳይሆን እንደ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እና የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ እንድናየው ያስገድዳል።
የትውልድ ቅርስ ማለት ያለፈውን ብቻ መጠበቅ አይደለም፤ ለሚመጣው ትውልድ የተሻለ መነሻ መፍጠርም እንጂ።
በዚህ መልኩ የባሕር በር ጉዳይ የአሁኑ ትውልድ በሰላማዊ መንገድ ሊያሳካው የሚገባ እና ለሚመጣው ትውልድ ሊያስረክበው የሚገባ የሀገር አቅም ነው።
የኢትዮጵያ ባሕር በር ማለት ወደ ባሕር መድረስ ብቻ ሳይሆን ወደ የተሻለ ኢኮኖሚ፣ የተሻለ ንግድ፣ የተሻለ ቀጣናዊ ትስስር እና የተሻለ የትውልድ እድል መድረስ ነው። ዛሬ የምንወስነው ውሳኔ የዛሬን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የነገዋን ኢትዮጵያ ይቀርጻል።
የዛሬን ጥቅም በማስጠበቅ፣ የነገን ትውልድ በማሰብ፤ ባሕር በርን ወደ ዘላቂ የሀገር አቅም መቀየር የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው።
በኢንቲሀድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: