Search

የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል የኢትዮጵያ ንጹህ ኤሌክትሪክ እና የቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር አዲስ ምዕራፍ

ረቡዕ ነሐሴ 27, 2018 170

ምስራቅ አፍሪካ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ላይ የምትገኝ ቀጣና እንደመሆኗ መጠን፣ አስተማማኝ እና ንጹህ የኃይል አቅርቦት ፍላጎቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

በዚህ ታሪካዊ የኃይል ሽግግር ወቅት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዋን፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮቿን እና ግዙፍ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንቶቿን በመጠቀም የጎረቤት ሀገራትን የኃይል እጥረት በመቅረፍ ረገድ ቀዳሚውን ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

የኤሌክትሪክ ኃይልን ለኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ በመሸጥ ረገድ እያሳየች ያለችው ታላቅ ስኬት ሀገራችንን የምስራቅ አፍሪካ የእውነተኛ የኃይል ማዕከል እያደረጋት ይገኛል።

ኢትዮጵያ በዋናነት በውሃ፣ በነፋስ፣ በጂኦተርማል እና በፀሐይ ብርሃን ላይ የተመሰረተ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ባለቤት ስትሆን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት የሀገራችንን የኃይል ማመንጨት አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

ይህ አቅም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለቀጣናው ሀገራት የሚተርፍ ንጹህና አነስተኛ ካርቦን አውጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያስቻለ ነው።

በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ የገባው 500 ኪሎቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለውን የኃይል ንግድ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

በተመሳሳይ መልኩ ከሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር ያለው የኃይል ትስስር የነዳጅ ወጪን በመቀነስና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ አምጥቷል።

የኃይል ላኪነቱ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ለሀገራችን አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፤ በሀገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ዘላቂ ሰላምና የጋራ እድገት ያጠናክራል።

በቀጣይም የኃይል መስመሮቿን ወደ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ለማስፋፋት የተያዙት ዕቅዶች ሀገራችን በቀጣናው የምትጫወተውን የኃይል አቅርቦት መሪነት የበለጠ የሚያጸኑ ይሆናል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለአካባቢያዊ ትስስር እና ለአረንጓዴ ልማት በማዋል የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከልነቷን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።

 

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: