ሀገራችን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ልዩ ከሚያደርጓት ጸጋዎች መካከል አንዱ የብዝኃ ማንነቶች ማማ መሆኗ ነው።
በዚህች ውብ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን የማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገሩ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ደማቅ ሀገራዊ ጌጦች መካከል አንዱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው ነባሩ የዳውሮ ብሔረሰብ፣ በየዓመቱ በወርኃ ነሐሴ መጨረሻ በድምቀት የሚያከብረው የዘመን መለወጫ ‘ቶኪ-በዓ’ በዓል ነው።
‘ቶኪ-በዓ’ የቀን መቁጠሪያ ሽግግር ብቻ አይደለም። የቀደሙት የዳውሮ አባቶች የነበራቸውን ጥንታዊ የከዋክብት እና የጨረቃ ዑደት መነሻ ያደረገ የረቀቀ የዘመን አቆጣጠር ዕውቀት፣ ከባህላዊ ዕሴቶች እና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ጋር አጣጥሞ የያዘ ድንቅ ሥርዓት ነው።
የዳውሮ ብሔረሰብ ይህንን በዓል ሲያከብር ዘመንን ለትውልድ ቀምሮ ከማሻገር ባለፈ፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ መፍለቂያነቱን ለዓለም በኩራት የሚያሳይበት ታላቅ ቀኑ ነው።
ይኸውም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውን እና በድንቅ የሕንፃ ጥበብ የታነጸውን የድንጋይ ክምር መከላከያ ግንብ (ሃላላ ኬላን) በገነቡት በንጉሥ ሃላላ (ካዎ ሃላላ) የሚመራው ታሪካዊ ማንነታቸው ሕያው ሆኖ የሚታሰብበት በመሆኑ ነው።
ይህ ታላቅ ቀን በዳውሮ ብሔረሰብ ዘንድ የምስጋና እና የተስፋ ዓርማ ነው። በዓሉ አሮጌውን ዓመት በሰላም፣ በጤና እና በደስታ ላሻገረው ፈጣሪ በጋራ ምስጋና የሚቀርብበት፣ መጪው አዲስ ዓመት ደግሞ የሰላም፣ የፍቅር፣ የምርታማነት እና የብልጽግና ዘመን እንዲሆን የጋራ ጸሎት እና መልካም ምኞት የሚሰማበት መንፈሳዊ ከፍታ ያለው ሥርዓት ነው።
ከዚህም ባሻገር ‘ቶኪ-በዓ’ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፣ የተቸገሩ እና አቅም ያነሳቸው ወገኖች የሚጠየቁበት የጥጋብ በዓል ነው። የዳውሮ ሕዝብ መለያ የሆነው ድንቅ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እና የአብሮነት እሴት ፍንትው ብሎ የሚታየውም ማንም ሰው ሳይራብ ማዕድ በሚጋራበት በዚህ ታላቅ ዕለት ነው።
የ‘ቶኪ-በዓ’ ሌላው አንጸባራቂ ገጽታ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያስጠብቅበት የራሱ የሆነ ጥልቅ የዳኝነት ሥርዓት መኖሩ ነው። በበዓሉ ወቅት ባህላዊ ዳኝነት እና የግጭት አፈታት ሥርዓት ይካሄዳል። የተጣላ ይታረቃል፣ ቂም ይረሳል፣ በበደል የተራራቀ ይቅርታ ተባብሎ በአዲስ መንፈስ ይቃቀፋል። ይህ ተግባራዊ የእርቀ-ሰላም ሥርዓት በዓሉን የሰላም፣ የእርቅ እና የአንድነት ሕያው መገለጫ ያደርገዋል።
በ‘ቶኪ-በዓ’ ውስጥ የታመቁት እነዚህ የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነት እና የአብሮነት እሴቶች ለዳውሮ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ የሰላም ባህል ግንባታ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ያላቸው ሚና እጅግ የጎላ ነው።
የሕዝቦችን አንድነት በሚገነባ መልኩ በጋራ የሚከበረው ይህ በዓል፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ይበልጥ የሀገራችን ውበት እና ጥንካሬ ሆኖ እንዲቀጥል ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
በዓሉ በዛሬው ዕለት በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በታላቅ ድምቀት እየከበረ ይገኛል። እንኳን ለዳውሮ ሕዝብ የዘመን መለወጫ ‘ቶኪ-በዓ’ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: