የዘመን መለወጫ ለኢትዮጵያውያን የቀን መቁጠሪያ ላይ ከሚሰፈር የቁጥር ሽግግር የዘለለ ጥልቅ ትርጉም አለው።
ይህ ወቅት ምድር በራሷ አንደበት የምትናገርበት፣ ሰማያት የብርሃን ተስፋን የሚፈነጥቁበት፣ የራቀ ዘመድ ከዘመዱ የሚገናኝበት የፍቅር እና የብሩህነት ወቅት ነው።
የክረምቱ ከባድ ደመና ተገፍፎ በጠራው የመስከረም ሰማይ ሲተካ፣ ኢትዮጵያውያንም ካለፈው የውጣ ውረድ ትዝታ ተላቅቀው በአዲስ መንፈስ ወደፊት የሚራመዱበት ታላቅ የሕይወት ምዕራፍ ይከፈታል።
አሮጌውን ዓመት በክረምቱ ጭጋግ ሸኝተን አዲሱን ዘመን በብራ ብርሃን ስንቀበል፣ በልባችን ውስጥ የሚፈጠረውን የነገን የማለም ስሜት ቃላት ሊገልጹት አይችሉም።
መስከረም ሲጠባ ምድራችን በክት ልብስ እንዳጌጠች ውብ ኮረዳ ቢጫ ቀሚሷን ትለብሳለች። የደፈረሱ ወንዞች ሲጠሩ፣ ሰማዩ በብርሃን ሲፈካ፣ ከዐደይ አበባ መፍካት ጋር መስኩ ሁሉ በውበት ሲደምቅ እንዲሁም እምቦሳዎች ሲቦርቁ... ይህ ሁሉ የዕይታ ድግስ በውስጣችን ያለውን የነገ ተስፋ አብሮ ያለመልመዋል።
ወራት ተቆጥረው አዲሱ ዓመት ሲመጣ፣ ከሰማዩ እና ከወንዞቹ መጥራት ጋር ተያይዞ የሚመነጨው መንፈስን የማደስ ኃይል እጅግ ጥልቅ እና ሕያው የተፈጥሮ ምሥክር ነው።
ይህ የተፈጥሮ እና የሰው ልጅ ውብ የዘመን መተካካት ከዕይታም ባለፈ ሌላ ትልቅ የሕይወት ፍልስፍናን ያወርሰናል።
ወቅቱ በክረምቱ ዝናብ፣ ብርድ እና ጭቃ ሳይበገሩ ያፈሰሱት ላብ እና የዘሩት ዘር ወደ ተስፋ ፍሬ የሚሸጋገርበት የሽልማት ጊዜ ነው።
በጭቃ እና በድካም ውስጥ የተዘራው ፍሬ በቅሎ እና አሽቶ የድካምን ዋጋ ሲያስገኝ፣ ተፈጥሮ ራሷ ትዕግሥትን፣ አይበገሬነትን እና ከጨለማ በኋላ ብርሃን መኖሩን በተግባር ታስተምረናለች።
ይህም እያንዳንዱ የሕይወት ፈተና ወደሚያብብ የተስፋ ፍሬ እንደሚቀየር የሚያረጋግጥልን የተፈጥሮ ቃል ኪዳን ነው።
እነሆ አዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋን ሰንቆ መጥቷል! ይህ ዘመን የጀመርነው መልካም ጥረት ሁሉ የሚያብብበት፣ የምንመኘው ሰላም፣ ፍቅር እና ደስታ ልክ እንደ ዐደይ አበባ ፈክቶ የሚታይበት እንዲሆን እንመኛለን።
አዲሱን የተፈጥሮ ብሩህነት ወደ ሕይወታችን አጋብተን፣ ይህንን የታደሰ ተስፋ ሰንቀን በአዲስ መንፈስ ወደተሻለ ነገ በጋራ እንጓዝ።
መልካም አዲስ ዓመት!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: