Search

የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" የዋዜማ ክዋኔዎች መካሄድ ጀመሩ

ቅዳሜ ነሐሴ 30, 2018 153

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት የተመዘገበው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በመቃረቡ፣ የበዓሉ ዋዜማ በልዩ ልዩ ማኅበራዊና ባህላዊ ክዋኔዎች በደመቀ ሁኔታ መከበር ጀምሯል።

በወላይታ የዘመን አቆጣጠር ቀመር መሠረት የዓመቱ የመጀመሪያ ወር የሆነው እና ታላቅ፣ በኩር ወይም የመጀመሪያ በሚል ትርጓሜ የሚታወቀው የጊፋታ በዓል፤ ከአሮጌ ወደ አዲስ ተስፋ፣ ከክረምት ወደ በጋ፣ እንዲሁም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሪያ ነው።

የበዓሉን መድረስ ተከትሎ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በዓሉን ለመቀበል ደማቅ የዝግጅት ክዋኔዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

የበዓሉ ዋዜማ የኅብረተሰቡን አብሮነት፣ አንድነትና የመተሳሰብ እሴት የሚያጎሉ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበት ወቅት ነው።

በዚህም እናቶች በቅቤ እቁብ የጀመሩትን ቁጠባ ሲያጠናቅቁ፤ አባቶች ደግሞ ዓመት ሙሉ የቆጠቡትን ገንዘብ ሰብስበው ከሦስት ወር በፊት የገዟቸውን የእርድ በሬዎች የማስቀለብ ሥርዓት በመፈጸም ላይ ናቸው።

በተጨማሪም ወጣቶች ለጉሊያ (ደመራ) የሚሆን እንጨት በመሰብሰብ እና በመከመር፣ እናቶች ደግሞ የእንሰት መፋቅ ሥነ-ሥርዓት በመከወን የበዓሉን መድረስ በማብሰር ላይ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ከበዓሉ አስራ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ልዩ ግብይት የሚከናወንባቸውና የበዓሉ ድምቀት የሆኑት ሀሬሀይቆ ቦቦዳ እና ጎሻ የተሰኙ ባህላዊ ገበያዎች ደምቀው መዋል ጀምረዋል።

ምርት በገፍ የሚቀርብበት የሀሬሀይቆ ገበያ፣ ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቁሳቁሶች የሚሸጡበት የቦቦዳ ገበያ፣ እንዲሁም የማህበረሰቡ አባላት በማለዳ ተነስተው የመጨረሻ ግብይት የሚያካሂዱበት የጎሻ ገበያ ለዋዜማው ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል።

ጊፋታ የዕርቅ እና የሰላም በዓል በመሆኑ፣ ማኅበረሰቡ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ዕዳዎችን በመክፈል እና አካባቢውን በማጽዳት በዓሉን በሙሉ ደስታ ለማክበር ዝግጅቱን አጠናክሯል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዋዜማው አከባበር አካል የሆነው እና በወላይታ ዞን የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን የማስጎብኘት ዓላማ ያለው "ጊፋታ ቱር" መርሐ ግብር በዚህ ሳምንት እየተካሄደ ይገኛል።

በትዕግስቱ ቡቼ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: