Search

የታላቋ ኢትዮጵያ ማንሰራራት፣ ዘመንን መዋጀት

ቅዳሜ ነሐሴ 30, 2018 257

ታሪክ የትውልዶች ቅብብሎሽ፣ የውድቀት እና የትንሣኤ ዑደት ነው። የሕዝቦች ታላቅነት የሚለካው በገጠማቸው ፈተና ብዛት ሳይሆን፣ ያንን ፈተና ተሻግረው በሚያሳዩት አይበገሬነት (የማንሰራራት) አቅም ነው።

ዛሬ ላይ ቆመን የኢትዮጵያን የቅርብ ዓመታት ጉዞ ስንመረምር፣ ሀገራችን ከዘመናት የእንቅልፍ እና የኋሊት ጉዞ ነቅታ፣ ወደ ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ እና የተስፋ አድማስ እየተሸጋገረች መሆኗን በግልጽ እንመለከታለን።

ከፈተና ወደ ግስጋሴ የማንኛውም ታላቅ ሀገር መሠረት የሚጸናው በፈተና እቶን ውስጥ ሲያልፍ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ያሳለፈችው የፈተና ዘመን በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ሀገራችን በውስጥ እና በውጭ ሕልውናዋን የሚፈታተኑ ከባድ ፈተናዎችን በተጋፈጠችበት ወቅት ላይ ነበረች። በተለይም የተለያዩ ግጭቶች እና ጦርነት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ እንዲሁም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ያስከተለው የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫና የፈጠሩት "የሦስትዮሽ መከራ" ሀገራዊ የለውጥ ጉዞን ለመግታት የሞከሩ ተግዳሮቶች ነበሩ።

ከዚህም ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋዎች ሀገራዊ አንድነትን ለመበጣጠስ እና ኢኮኖሚውን ለማድቀቅ የተቃጡ ፈተናዎች ነበሩ።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና አመራር እነዚህን ሕልውናን የሚፈታተኑ ፈተናዎች በጽናት ከመመከት አልፈው፣ አንዳንዶቹን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ሀገራዊ ግስጋሴውን አስቀጥለዋል።

ይህ በእሳት ውስጥ አልፎ የነጠረ የማይበገርነት ማረጋገጫ፣ ሀገራችንን ከውድቀት ስጋት ታድጎ ወደ ላቀ የልዕልና ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው። አሁን ያለንበት ጊዜ ዜጎች በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ከሚፈረጁበት የጠበበ ምኅዳር ወጥተን፣ ሕዝቦች ከመጠፋፋት ወደ መተባበር የዴሞክራሲ ልምምድ የተሸጋገሩበት አዲስ የዐርበኝነት ትውልድ ግንባታ ዘመን ነው።

የአሁኑ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ የለውጥ ጉዞ በታሪክ ትልልቅ ማዕበሎችን አልፈው ከገነኑ ታላላቅ ሀገራት አነሳስ ጋር በእጅጉ ይስተካከላል። አውሮፓውያኑ በአብርኆት ዘመን የሐሳብ ልዕልናን፣ ምክንያታዊነትን እና ተቋማዊ ግንባታን በማስቀደም ከጨለማው ዘመን እንደወጡ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ከስሜታዊነት እና ከፅንፈኝነት ወጥታ "ገቢር ነበብነት" (Pragmatism) እና "መደመር" በሚሉ አዳዲስ እና ሀገር-በቀል ዕሳቤዎች ላይ ተመሥርታ የፖለቲካ ስብራቷን እየጠገነች ትገኛለች።

ጣሊያን በሕዳሴዋ የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ሕንፃ እና የሥልጣኔ ማማ ሆና ዳግም እንደተወለደችው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ዛሬ "ከተሞች በአዲስ ምናብ" በተሰኘው መሪ ቃል በጀመረችው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተሞቿን እያዘመነች፣ እያስዋበች እና ለነዋሪዎች ምቹ እያደረገች ዳግም ልደቷን እያበሰረች ነው።

በተጨማሪም ጁሴፔ ጋሪባልዲ የተበታተነችውን ጣሊያን በአንድነት እና በጽኑ የዐርበኝነት ስሜት እንዳዋሐዳት ሁሉ፣ የኢትዮጵያም የለውጥ ጉዞ ብሔርን ማዕከል ካደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ ወደ ሐሳብ እና መርሕ መር ፖለቲካ በመሸጋገር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ያጸና ሥርዓት እየገነባ ይገኛል።

ይህ ጉዞ ከፋፋይ እና ነጠላ ትርክቶችን በማርገብ፣ የወል ሀገራዊ ዕሴቶችን የሚያሰርጽ እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

የስምንት ዓመቱ ሽግግር ከመጋቢት 24 ቀን 2010 . ጀምሮ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተደረገው ሽግግር ኢትዮጵያን አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ያደረገ ወሳኝ ግስጋሴ ነው።

በዚህ የለውጥ ጉዞ፣ ኅብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር፣ ፖለቲካዊ መገለልን ያስቀሩ የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙበት አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ተፈጥሯል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አፍራሽ ከሆነው እና እግር ከወርች አስሮ ከያዘው የልዩነት እና የጥላቻ ትርክት በመውጣት፣ አሰባሳቢ ወደሆነው "የብሔራዊነት ትርክት" በመሸጋገር ላይ ይገኛል።

የሽግግሩ ዓመታት በኢኮኖሚውም ረገድ ተዓምር ሊባል የሚችል ትራንስፎርሜሽን የታየባቸው ናቸው። ሀገራችን ለዘመናት የረኃብ ተምሳሌት አድርጎ ያስቆጠራትን የታሪክ ጠባሳ በመቀየር፣ ከስንዴ ልመና እና ገቢ ሰጪነት አላቅቃ ወደ ውጭ ላኪነት የተሸጋገረችበት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደማቅ የታሪክ ገጽ ነው።

በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ዓለም አቀፍ ተምሳሌት የሆነው "የአረንጓዴ ዐሻራ" ንቅናቄ፣ እንዲሁም የሌማት ትሩፋት የዚሁ ስምንት ዓመት የለውጥ ፍሬዎች ናቸው።

የኢትዮጵያውያን የሉዓላዊነት እና የብልጽግና ማሳያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የውኃ ሙሌቱን አጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የዚሁ ጽናት ውጤት ነው። በዲፕሎማሲውም መስክ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ እና የባሕር በር ጥያቄን በፍትሐዊነት በማንሳት የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖዋን አጉልታለች።

ዘመንን መዋጀት የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ የዘመናትን ዕዳ ለመክፈል፣ የሀገራችንን ከፍታ ለመመለስ እና ብሩህ የወደፊት ጊዜን ለማረጋገጥ ወስኖ ተነሥቷል።

ይህ ትውልድ በትናንት በደሎች ዛሬ ላይ ጥፋተኛ ከመፈለግ ወጥቶ፣ የትናንት ጥፋቶችንም ሆነ ልማቶችን እንደ የጋራ ታሪክ በመውሰድ ዛሬን እና ነገን ብሩህ ለማድረግ ቆርጧል። ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ድሎች የኢትዮጵያ ትንሣኤ አሐዱ ብሎ መጀመሩን የሚያበስሩ እንጂ እንደ ፍጻሜ የሚታዩ አይደሉም።

ዘመንን መዋጀት ማለት ያመለጠንን የሥልጣኔ ባቡር በፈጣን ዕርምጃ ተራምዶ መድረስ ማለት ነው። መጋቢት ድልን እንደወለደች ሁሉ፣ ይህ ትውልድም ድሎቹን አጽንቶ ለቀጣዩ ትውልድ በሁሉም ዘርፍ የበለጸገች እና የከበረች ሀገር ለማስረከብ ቃል ኪዳኑን እያደሰ ይገኛል።

በማይበገር ጽናት፣ እያደገ በመጣ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ እና እየፈረጠመ ባለ ኢኮኖሚ፣ ኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ሆና ትቀጥላለች። የኢትዮጵያ ብልጽግና ዕውን መሆኑ አይቀሬ ነው፤ ጉዟችንም አያጠራጥርም ወደ ብርሃን ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: