Search

ሀገራዊ አቅም እና የኢትዮጵያ ከፍታ

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 200

የኢትዮጵያ ማንሰራራት ከውድቀት መነሳት ብቻ አይደለም፤ ለዘመናት ተጭኖ የነበረውን የተስፋ መቁረጥ እና የጥገኝነት ሥነልቦና ሰብሮ፣ የራስን እውነተኛ ብሔራዊ አቅም እና ከፍታ ማብሰር ነው።

ለዘመናት በዘለቀው የስጋት እና የእርዳታ ጥገኝነት አሠራር ምክንያት፣ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ታላቅ ተፈጥሯዊ ጸጋ አውጥተው ለመጠቀም እንዳይደፍሩ አንችልም በሚል ሥነልቦናዊ ሰንሰለት ታስረው ቆይተዋል።

የመደመር እሳቤ ግን ይህንን የተሳሳተ የታሪክ ትርክት በመቀየር ሀገር በቀል አቅምን ወደ ሁለንተናዊ ዕድገት ያሸጋገረ አዲስ የልማት እና የሉዓላዊነት ምዕራፍ ከፍቷል።

በታቀደላቸው ጊዜ ፕሮጀክቶችን አለማጠናቀቅ በቀደሙት ጊዜያት ብሔራዊ ስጋት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ይህ ስብራት ሙሉ በሙሉ ተሰብሮ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ የታሪክ አዲስ ምዕራፍ መጻፍ ጀምራለች።

የዓለም አቀፍ ተቋማትን እጅ ሳትጠብቅ በዜጎቿ ወዝ እና የጋራ አስተዋጽኦ የተገነባው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ ብሔራዊ የኃይል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የትልቅ ማንሰራራት ህያው ምልክቶች ሆነዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ የቀጣናውን ሀገራት በኃይል በማስሳሰር የጋራ እድገትን እውን የሚያደርጉ ስትራቴጂካዊ ሀብቶች ናቸው።

ከኃይል ማመንጨት ጎን ለጎን፣ የአፍሪካ ትልቁ የመንገደኞች እና የካርጎ ማዕከል የሚሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶች መስፋፋት የኢትዮጵያን አህጉራዊ የትራንስፖርት የበላይነት ወደ አዲስ የልዕልና ማህተም ያሸጋገሩ ናቸው።

በተጨማሪም ለዘመናት በመሬት ስር ተቀብሮ የነበረውን ተፈጥሯዊ ሀብት አውጥቶ ማቀነባበር፣ የምግብ ዋስትናን በሀገር ውስጥ ምርት ማረጋገጥ እና የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን በሀገር ውስጥ የመገንባት ጥረት የውጭ ጥገኝነትን በማስቀረት ብሔራዊ የኢኮኖሚ ነፃነትን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።

እነዚህ ግዙፍ ሥራዎች ሲከናወኑ ትልቁ የማንሰራራት ማረጋገጫ የግንባታዎቹ መጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ በዜጎች እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የተፈጠረው ጥልቅ እይታ ነው።

ኢትዮጵያ በገዛ ሀብቷ፣ በዕውቀቷ እና በሕዝቧ አስተዋጽኦ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ እንደምትችል በተግባር በማሳየት የጸና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አድርጋለች።

ኢትዮጵያ የእርዳታ እጅ ዘርጊ ምሳሌ ከመሆን ወጥታ የራሷን የልማት እጣ ፈንታ በራሷ የምትወሰን የማይበገር የቀጣናው የኢኮኖሚ ሞተር መሆኗን አስመስክራለች።

"አይደፈርም" የሚለውን የተረጂነት እና የእንቅፋት አጥር መስበር ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ትልቁ ሀገራዊ የማንሰራራት ውርስ ነው።

የዛሬው ትውልድ ከትናንቱ የተስፋ መቁረጥ ጥላ ወጥቶ፣ በማንኛውም የልማት መስክ ላይ "እንችላለን" የሚል የጸና ሥነልቦናዊ እምነት እንዲላበስ ተደርጓል።

ይህ አዲስ አካሄድ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ከፍታ እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያበስር ወርቃማ የማንሰራራት ምዕራፍ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: