ኢትዮጵያ ለዘመናት ተጫኖባት የነበረውን የምግብ እርዳታ ጥገኝነት ታሪካዊ ጠባሳ በመሻር በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የስንዴ አምራች እና ላኪ የመሆን ታላቅ ጉዞዋን በላቀ ስኬት እውን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የተመዘገቡት ስኬቶች የግብርና ምርታማነት ማደግ ማሳያዎች ብቻ አይደሉም።
ይልቁንም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ከፍታ የራስ አቅም ብቃት ማረጋገጫ እና የማንሰራራት ዘመንን የሚያበስሩ የታሪክ ማኅተሞች ናቸው።
ለአያሌ ዓመታት የዘለቀው ኋላቀር የግብርና አሠራር ኢትዮጵያን በክረምት ዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ እንድትሆን እና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ አመራረት እንድትወሰን አድርጓት ቆይቷል።
ነገር ግን በመደመር እሳቤ የተቃኘው አዲሱ የእድገት አቅጣጫ ይህንን ለዘመናት የዘለቀ የረሃብ እና የስጋት ሰንሰለት ሰብሮታል።
ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በመስኖ አውታሮች በማስተሳሰር፣ ቀደም ሲል በበጋ ወቅት አልምተው የማይጠቀሙባቸውን ሜዳዎች ወደ አረንጓዴ የምርት ማዕከልነት መቀየር ተችሏል።
በተለይም ምርጥ ዘርን፣ ዘመናዊ የኩታ ገጠም አሠራርን እና ሜካናይዜሽንን በስፋት በመጠቀም በሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ተችሏል።
ቁጥራዊ ማሳያዎች እንደሚረጋገጡት በ2016 የምርት ዘመን ብቻ ከ230 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ማምረት ተችሏል።
ከዚህ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 107 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታሉ በመስኖ ከለማ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው 123 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ በአነስተኛ አርሶ አደሮች የ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ልማት የተሰበሰበ ነው።
በ2009 ዓ.ም በጠቅላላው 54 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ የነበረው የስንዴ ምርት በአጭር ዓመታት ውስጥ በአራት እጥፍ በላይ ማደጉ የለውጡን ፈጣን ምጥቀት ያሳያል።
በ2017 የምርት ዘመንም አጠቃላይ ምርቱን ወደ 300 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በዚህም ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ከውጭ ስንዴ ታስገባ የነበረበት የታሪክ ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል።
የውስጥ የስንዴ ፍላጎትን በራስ ምርት መሸፈን መቻሉ ለስንዴ ግዢ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማዳን ለሌሎች መሠረተ ልማቶች እና ኢንዱስትሪዎች እንዲውል አስችሏል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ከውጭ ማስገባትን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት እና ለዓለም አቀፍ ገበያዎች ማቅረብ የጀመረችበት አዲስ የላኪነት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ከዚህ በተጨማሪም ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የወተት፣ የዶሮ፣ የማር እና የሥጋ ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ እና የሥርዓተ-ምግብ ሉዓላዊነት በተሟላ ደረጃ ለማረጋገጥ አስችሏል።
የስንዴ ሉዓላዊነት እና የሌማት ትሩፋት ያመጡት ትልቁ ስኬት በቁጥር ከሚገለጸው ምርት ባሻገር፣ በዜጎች ሕሊና ውስጥ የተፈጠረው ጥልቅ የሥነ-ልቦና ፈውስ ነው።
ለአያሌ ዓመታት በውጭ እርዳታ ጥገኝነት ሥር የነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ በራሳቸው ላብ እና ጥረት የራሳቸውን ማዕድ መሸፈን እንደሚችሉ በተግባር ማረጋገጣቸው የብሔራዊ ታላቅነት እና የ“እንችላለን” መንፈስ በሰፊው እንዲሰርጽ አድርጓል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ መቻሏ ከግብርና ስኬት በላይ የሆነ ትርጉም አለው።
ለዘመናት የታሰረችበትን የተረጂነት ሰንሰለት በጥሳ የራሷን ዕድል በራሷ እጅ መጻፍ መጀመሯን እና ወደ ታሪካዊ ልዕልናዋ በመመለስ ላይ መሆኗን የሚያበስር ታላቅ የድል ጉዞ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: