Search

"አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ የምትሰጥ መሪ መሆን አለባት" - ዋና ጸሐፊ ክላቬር ጋቴቴ

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 119

በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው የፋይናንስ ድጋፍ ሊያድግ እና ቃል የተገባው ፋይናንስ ሊሰጥ እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ዋና ጸሐፊ ክላቬር ጋቴቴ አሳሰቡ።

አፍሪካ በአየር ንብረት ዙሪያ ጥቅሟን ከማስከበር ባለፈ ውሳኔ ሰጪነቷን እና መሪነቷን ማጠናከር እንዳለባትምተጠቁሟል።

14ኛው የአየር ንብረት ለውጥ እና ልማት በአፍሪካ ጉባኤ "ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር፡ የቤሌም-አንታሊያ-አዲስ አበባ ፍኖተ ካርታ" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የጉባኤው ዋና ዓላማ አፍሪካን ከማስከበር ባለፈ የአፍሪካን ውሳኔ ሰጪነት እና መሪነት ማጠናከር ነው ተብሏል።

ይህ መድረክ አህጉሪቱ 31 የአየር ንብረት ጉባኤ ጠንካራ መፍትሔዎችን እንድታዘጋጅ እና 2027 ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው 32ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ የጋራ ፍኖተ ካርታ እንድትቀርጽ እንደሚያግዛትም ነው የተገለፀው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ዋና ጸሐፊ ክላቬር ጋቴቴ፣ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ዙሪያ አቋሟን በማንፀባረቅ መሪነቷን ማሳደግ አለባት ብለዋል።

አፍሪካ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ያላት ልቀት ድርሻ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም በከፍተኛ ደረጃ ለጉዳት መዳረጓን አንስተዋል።

በዚህም ለአህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የሚደረገው ፋይናንስ ሊያድግና ቃል የተገባው ፋይናንስ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሁልጊዜ "ተጎጂ" ብቻ ሆና መቅረብ የለባትም፤ ይልቁኑ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኃይል፣ ማዕድናትና የሰው ኃይል አቅም በመጠቀም ከተስፋ ቃል ወደ ተግባር የሚሻገሩ አቅምን ያገናዘቡ የፋይናንስና የልማት መፍትሄዎችን ለዓለም ማቅረብ አለባት ብለዋል።

በዓባዲ ወይናይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: