Search

የኢትዮጵያ ማንሰራራት፦ ሉዓላዊነትን በላብ እና በምርታማነት የማጽናት ምዕራፍ

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 126

ኢትዮጵያ በታሪክ ውጣ ውረዶች እና በዘመናት ፈተናዎች ውስጥ በብስለት አልፋ፣ ለከፍታዋ እና ለገናናነቷ የሚመጥነውን የታላቅነት እና የማንሰራራት ጉዞ ጀምራለች።

አሁን ላይ በታሪካችን አይተን የማናውቃቸውን አዳዲስ ሀሳቦች ወደ ተግባር በመቀየር እና ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ እናት ሀገርን አጽንተን ለትውልድ እንደምናስረክብ በተግባር እያሳየን እንገኛለን።

በተለይም የጳጉሜን ወር ስንቀበል ያለፈውን የምንገመግምበት፣ ክፍተታችንን የምናርምበት እና ለቀጣዩ የብልጽግና ጉዟችን ተስፋ የምንሰንቅበት ልዩ ታሪካዊ መድረክ ነው።

የዘንድሮው የጳጉሜ ቀናትም "የኢትዮጵያ ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል መከበሩ፣ ሀገራችን ከነበረችበት አዝጋሚ ጉዞ ተላቃ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአገልግሎትና በቱሪዝም ዘርፎች እያስመዘገበች ያለውን ሁለንተናዊ የሪፎርም ስኬት የሚያንጸባርቅ ነው።

ታሪካችንን ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፣ ኢትዮጵያውያን የህልውና አደጋ ባጋጠመ ቁጥር ውድ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።

21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ይህ አውድ እና መንገዱ ተቀይሯል። በዚህ ውስብስብ ዘመን በደም የተከበረ ነፃነት እና በአጥንት የተረጋገጠ ሉዓላዊነት በላብ ካልጸና፣ ጠንክሮ በማምረት ካልታጀበ ውጤቱ የታሪክ ተናጋሪነት ብቻ ሆኖ ይቀራል።

የላብ ዋጋ ጠንካራ ተጽዕኖን የሚፈጥርበት ጽኑ መንገድ በመሆኑ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የህልውናዋ ማረጋገጫ ዳርድንበርን ከመጠበቅ ባሻገር ከምግብ ጥገኝነት መላቀቅ፣ ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚ መሰረት መገንባት እና በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን ነው።

ይህንን የላብ እና የትጋት ፍልስፍና በተግባር ያሳየንበት ትልቁ ማሳያ፣ አይችሉም የሚለውን ትርክት የሰበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው።

ያለማንም የውጭ እርዳታ፣ በራሳችን ሀብት፣ ድካም እና ዕውቀት የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ እና ተከታታይ የኃይል ማመንጫዎችን ወደ ሥራ በማስገባት ለምሥራቅ አፍሪካ ብርሃን ፈንጥቀናል። ግዙፍ ማምረቻዎቻችንንም በታዳሽ ኃይል ለማንቀሳቀስ አቅም ፈጥረናል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት እና ከእጅ ወደ አፍ አኗኗር ወጥቶ፣ ዓመቱን ሙሉ በማምረት ወደ ገበያ ተኮር ስርዓት ተሸጋግሯል።

የሌማት ትሩፋት፣ የክላስተር ግብርና እና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ያጸደቅነው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄዎች የምግብ ሥርዓታችንን ከማዘመንም አልፈው፣ የዜጎችን የስራ ባህል ቀይረዋል።

በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ትርፍ አምራችነት ኢኮኖሚያችንን በእጅጉ ደግፎታል።

በማዕድን ዘርፉም እንደ ወርቅ፣ ኦፓል እና የድንጋይ ከሰል ያሉ ሀብቶችን ከህገ-ወጥ አሠራር በማላቀቅና የድንጋይ ከሰል እጥበትን ሀገር ውስጥ በማስፋፋት የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ የኢኮኖሚያችን ዋልታ እየሆኑ ነው።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም ተፈጥሯዊ ሀብትን ከማስጎብኘት ባለፈ፣ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመጥኑ እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሃላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ እና የንጋት ሐይቅ ያሉ ግዙፍ መዳረሻዎችን በላቀ ደረጃ አልምቷል።

ከዚህም ባሻገር በአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ስኬት እና በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራ አማካኝነት ሀገራችንን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ በማሸጋገር ላይ እንገኛለን።

እነዚህን ድሎች ስንመለከት፣ ለዘመናት የነበሩ ቁርሾዎች እና የታሪክ ስብራቶች የልማት ህልማችንን እንዴት ወደ ኋላ እንደጎተቱ በተግባር አይተነዋል።

ይህንን ታሪክ ለመቀየር እና ዘላቂ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ሰፊ ውይይቶችን ማካሄዱ የዘመናችን ትልቁ ድል እና የማንሰራራታችን ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

በዚህ የማንሰራራት መንፈስ ነው የዘንድሮዉን የጳጉሜ ቀናት የምናከብረው። በአዲሱ ዓመት፣ ምርታማነታችንን አጎልብተን፣ ኅብረታችንን አጠናክረን፣ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ሁላችንም በትጋት ልንሠራ ይገባል! ነጋችንን በዛሬው ስኬታችን ላይ በላባችን እንገነባለን!

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: