ኢትዮጵያ በ2030 የንፁህ ኃይል ማመንጨት አቅሟን 13 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ አቅዳ እየሠራች መሆኑን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ አስታወቁ።
ፕሬዚዳንቱ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ (AIM Congress) ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የትሥሥር ማዕከልነት ለማረጋገጥም በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያን እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የዓለም ኢኮኖሚ መዋቅር እና የቴክኖሎጂ ሁኔታዎች በመሠረታዊነት እየተለወጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ተለዋዋጭ የሆኑት የጂኦ-ፖለቲካ ሁኔታዎች የዓለምን የንግድ ዕሴት ሰንሰለት እየወሰኑ መምጣታቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ እነዚህ አዳዲስ ክስተቶች በአፍሪካ ላይ ፈተናዎችን ቢያመጡም፣ በሌላ በኩል ደግሞ አኅጉሪቱ ወደ ውስጥ እንድትመለከት እና የራሷን አቅም እንድትጠቀም ሰፊ ዕድል መፍጠራቸውን አብራርተዋል።
ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ ኅብረት በኩል የዚህ ተለዋዋጭ ዓለም ተመልካች ሳይሆኑ ዋነኛ ተሳታፊ እና ሥርዓት ገንቢ ለመሆን የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ተከታታይ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞችም ከዚሁ አኳያ የተቃኙ መሆናቸውን እንዳስረዱ ኢዜአ ዘግቧል።
አፍሪካ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ያላትን የስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ዕድሎች አሟጣ ለመጠቀም አምስት ዋና ዋና ተግባራትን ማከናወን እንዳለባት ፕሬዚዳንት ታዬ በንግግራቸው ዘርዝረዋል፦
የንፁህ ኃይል ልማት፦ አፍሪካ የጋራ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማምጣት ከንፋስ፣ ከፀሐይ፣ ከአንፋሎት እና ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ በሚገኝ ንፁህ ኃይል ላይ ትኩረት ማድረግ አለባት። ኢትዮጵያ 60 ሺህ ሜጋ ዋት ንፁህ ኃይል የማመንጨት ዕምቅ አቅም ያላት ሲሆን፣ እ.አ.አ በ2030 የማመንጨት አቅሟን 13 ሺህ ሜጋ ዋት በማድረስ ለምሥራቅ አፍሪካ እና ለሌሎች ሀገራት የሚቀርበውን የኃይል አቅርቦት በስፋት ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች።
የግብርና ልማት፦ የአፍሪካ ሀገራት በግብርናው ዘርፍ ላይ ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል። ለዚህም ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በስንዴ ምርት ያስመዘገበችው እመርታ ለአኅጉሪቱ በተሞክሮነት ቀርቧል።
የማዕድን ሀብት አጠቃቀም፦ አኅጉሪቱ ከወርቅ ጀምሮ እስከ ኮባልት እና ሊቲየም ያሉ ማዕድናትን በሚገባ መጠቀም አለባት። ኢትዮጵያም 'ታንታለም' የተባለውን ማዕድን በማምረት በዓለም 6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ተገልጿል።
መሠረተ ልማት እና አኅጉራዊ ትሥሥር፦ አፍሪካ የመሠረተ ልማት እና የዲጂታል ትሥሥርን ማስፋፋት አለባት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ረገድ የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ለአብነት ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የትሥሥር ማዕከልነቷን ይበልጥ ለማጽናት በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የቢሾፍቱን አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባች መሆኗን አስታውቀዋል። በተጨማሪም 3.4 ትሪሊዮን ዶላር የገበያ አቅም ያለውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሰው ኃይል እና የዲጂታል ክህሎት፦ የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን ወጣት የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም አለባቸው። ኢትዮጵያም በተለይ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ወጣቶችን ለማብቃት የ"ኮደር" ሥልጠና እየሰጠች መሆኗን ገልጸው፣ ለዚህ ኢኒሼቲቭ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በዱባይ በመካሄድ ላይ በሚገኘው በዚህ ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት እና የምርምር ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን፣ ጉባኤው ከነገ በስቲያ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: