በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ እና የተቋሙ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ እንደገለጹት በነገው ዕለት ጳጉሜን 3 የሚከበረው "የጽናት ቀን" የደኅንነት እና ጸጥታ ተቋማት የደረሱበትን ጠንካራ ቁመና በሚዘክርና ለቀጣይ ሥራም በሚያበረታታ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።
የደኅንነት እና ጸጥታ ተቋማት ማንኛቸውንም ፈተናዎች እና አደጋዎች በጀግንነት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ አንድነት፣ የአየር ክልል እና የየብስ ግዛት ማስከበር መቻላቸውን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ ገልጸዋል።
ሠራዊቱ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የተደቀኑ ማንኛቸውንም ፈተናዎች እና አደጋዎች በጀግንነት የመመከት እና ብሔራዊ ሉዓላዊነትን፣ የሕዝብ አንድነትን፣ የአየር ክልል እና የየብስ ግዛትን የማስከበር ታሪካዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታጥቀው የሀገርን ዳር ድንበር እና የሕግ የበላይነት እያስከበሩበት ያለውን ቁመና በሚያሳይ መንገድ ቀኑ እንደሚከበር ጠቁመዋል።
ተቋማቱ ያከናወኗቸውን መልካም ሥራዎች በማንሳት፣ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የብጥብጥ ሥጋት ተላቅቃ ወደ ተሻለ የሰላም እና የአንድነት ደረጃ የምትሸጋገርበትን አቅጣጫ ለመላው ሕዝብ በወጉ በማብራራት ጭምር ይከበራል ነው ያሉት።
የመከላከያ ሠራዊት በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ላይ የተገነባ፣ የሀገር ዋልታ እና ትልቅ ባለውለታ ተቋም በመሆን ብሔራዊ ሉዓላዊነትን ማስከበር መቻሉን አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም አደረጃጀቱን ዘመናዊ በማድረግ እና በቴክኖሎጂ በመታጠቅ ወንጀልን የመከላከል፣ የመመርመር እና ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ሌሎች የደኅንነት ተቋማትም ራሳቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰው ሠራሽ አስተውሎት በማደራጀት ሀገርን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ተነስቷል።
ነገ ጳጉሜን 3 የሚከበረው "የጽናት ቀን"፤ ለሰላም እና ደኅንነት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የጸጥታ አካላት ላበረከቱት አገራዊ አገልግሎት ምስጋና የሚቀርብበትና ለቀጣይ ተልዕኮ በጽናት እንዲዘጋጁ ጥሪ የሚተላለፍበት ዕለት ይሆናል።
በሳራ ሳህለስላሌ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: