ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ የዓለም አቀፍ ቁሳዊ እና የማይጨበጡ ቅርሶች ባለቤት፣ የሰው ዘር መገኛና የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ምድር ናት።
በአሁኑ ወቅት በዘርፉ እየታየ ያለው ፈጣን ማንሰራራት እና ተጨባጭ ዕድገት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ እየጻፈው ይገኛል።
ከድንቅ የተፈጥሮ መልክአ-ምድር እስከ ጥንታዊ ቅርሶች፣ ከባህላዊ እሴቶች እስከ ዘመናዊ የከተማ መስህቦች የተዘረጋው የቱሪዝም ሀብት ከቃል አልፎ የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ሞተርነቱን እያስመሰከረ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተወሰዱ ስትራቴጂያዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የገበታ ለሀገር እና ለትውልድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የከተሞች ኮሪደር ልማት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ካርታ ላይ ተራጭ የጉዞ መዳረሻ አድርገዋታል።
እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ ያሉ ግዙፍ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ እና ለተገልጋይ ክፍት መሆን፣ ከግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ የበረራ መረብ ጋር ተጣጥሞ የጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ አድርጓል።
ይህ በዘርፉ የተመዘገበው መነቃቃት የኢኮኖሚ መዋቅሩን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን ከመጨመሩ ባሻገር፣ እንደ ሆቴል እና እንግዶችን የመቀበል አገልግሎት፣ አቪዬሽን እና ትራንስፖርት፣ የባህል እና እደ-ጥበብ ምርቶች እንዲሁም አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማት በፍጥነት እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል።
ይህም ለብዙ ሺህ ዜጎች፣ በተለይም ለወጣቶች እና ለሴቶች አስተማማኝ የሥራ ዕድል በመፍጠር የአካባቢ ማኅበረሰቦችን የገቢ አቅም በተጨባጭ አሳድጓል።
ከዚህም በተጨማሪ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለዘላቂ ልማት ትኩረት የሰጡ የኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክቶች፣ የፓርኮች ልማትና የከተሞች ኮሪደር ማሻሻያዎች የመሠረተ ልማት ጥራቱን በማዘመን የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ እና አጠቃላይ ወጪ ከፍ አድርገውታል።
የቅርሶች እንክብካቤ ከኢኮኖሚ ጥቅም ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ መደረጉ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን ከመጠበቅ ባሻገር ዘላቂ የገቢ ምንጭነትን አረጋግጧል።
የቱሪዝም ዘርፉ ማንሰራራት የኢትዮጵያን አወንታዊ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉልህ ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ እየተመዘገበ ያለውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገትና የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ጠንካራ መሠረት እየሆነ መጥቷል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: