Search

ለታሪካዊቷ ጎንደር የተበረከተ ስጦታ፦ መቻላችንን ያረጋገጠው የመገጭ ግድብ

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 163

18 ዓመታት ያክል በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ያለፈው የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ግድብ ፕሮጀክት፣ በአሁኑ ወቅት 94 በመቶ የግንባታ አፈጻጸም ላይ በመድረስ ወደ ታሪካዊ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ይህ ስኬት ለረጅም ጊዜ የዘገዩ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ የመንግሥትን የፖሊሲ ቁርጠኝነት እና የማስፈጸም አቅም በተግባር ያረጋገጠ ትልቅ ማሳያ ነው።

2.4 ቢሊዮን ብር በጀት ተጀምሮ በተቋራጮች አቅም ማነስ፣ በፋይናንስ አቅርቦት እጥረት እና በተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጦች ምክንያት ፕሮጀክቱ ለዓመታት መጓተቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ አሁን ይህ ግዙፍ ሥራ በመዋቅር ማስተካከያ እና ብቃት ባላቸው ሀገር በቀል ተቋራጮች አስደናቂ ትጋት ወደ መገባደጃው ደርሷል።

በተለይም ፕሮጀክቱ ወደ ሀገር በቀል ኮንትራክተር ከተዘዋወረ በኋላ ግንባታው የተፋጠነበት ሒደት በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ትልቅ ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል።

በዕቅድ እና በቁርጠኝነት ከተሠራ የዘገዩ ፕሮጀክቶችን በቀን እና በሌሊት ፈረቃ በማፋጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማረጋገጫ ሆኗል።

በውኃ ሀብት አጠቃቀም ረገድም የተፈጥሮ ጸጋችንን ለአግሮ-ኢንዱስትሪ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለከተሞች የውኃ አቅርቦት አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚቻል ግድቡ በተግባር እያሳየ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ እስከ 185 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም አለው።

በአሁኑ ወቅት 33 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመያዝ በተጠናቀቁት የመስኖ ማውጫ ክፍሎች በኩል በቀን 5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እየለቀቀ መሆኑ ፕሮጀክቱ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ያመላክታል።

የዚህ ግድብ መጠናቀቅ ለታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያለው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው። ለከተማዋ ነዋሪዎች አስተማማኝ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን በማረጋገጥ የዘመናት የውኃ እጥረትን የሚቀርፍ ሲሆን፣ የውኃ ወለድ በሽታዎችንም በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።

ከዚህም ባለፈ የከተማዋን የሆቴል፣ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት የሥራ ዕድል ፈጠራን ያሰፋል።

በሌላ በኩል በደንቢያ እና በጎንደር ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች 17 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ያስችላል።

ይህም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ በማምረት የኢኮኖሚ አቅሙን እንዲያሳድግ እና የምግብ ዋስትናውን በዘላቂነት እንዲያረጋግጥ ትልቅ መሠረት ይጥላል።

ከነዚህ ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች ባሻገር ፕሮጀክቱ ትልቅ ሥነ ምኅዳራዊ ፋይዳ አለው።

በመገጭ ወንዝ በኩል ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባውን ከፍተኛ ደለል እና የአፈር እጥበት በመግታት ሐይቁ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በአጠቃላይ የመገጭ ግድብ ወደ ፍጻሜ መቃረብ በጽናት እና በተገቢው አመራር ከተሠራ የማይታለፍ ተግዳሮት እንደሌለ የሚያስተምር፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር እና የከተሞች ልማት ስኬት ማሳያ ይሆናል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: