ኢትዮጵያ የብዝኃ ማንነቶች ድምር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩበት የአየር ንብረት እስከ አመጋገባቸው፤ ከአመራረታው እስከ አለባበሳቸው፤ ከሃይማኖታቸው እስከ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው በርካታ ብዝኃነቶች ያስጌጧቸዋል፡፡ የእነዚህ ብዝኃነቶች ድምር ደግሞ የኢትዮጵያ የማድረግ ዐቅም ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን ብዝኃነት ለዘመናት የማይታረቁ የልዩነትና ግጭት ምንጭ ተደርጎ እንዲታይ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ያለመታከት ሠርተዋል፡፡ በዚህም በየዘመኑ የታዩ ስኬታማ ድሎችን በአጭር እየቀጩ ኢትዮጵያን የማይገባት ደረጃ ላይ እንድትገኝ ለማድረግ ጥረዋል፡፡ ይህ ትውልድ ግን የጠላቶቻችን ምኞትና የብዝኃነትን ዐቅም የተረዳ፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ ባለታሪክ ለመኾን የልዩነት ሰንኮፎቹን በምክክር ለመንቀል ወስኗል፤ የጋራ ዕጣ ፋንታዉን በጋራ ተልሟል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን የከፍታ ጉዞን ነጠብጣብ እንዳይኾን መሥመር አስይዘነዋል፡፡ ችግሮቻችንን እና የግጭት ምንጭ ኾነዉ ለባዕዳ መግቢያ ቀዳዳ፣ ለባንዳ መሹለኪያ የነበሩ ክፍተቶችን ለመድፈን በጋራ መክረናለ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ ትግል ያነበሩት የለውጥ መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት እየደረጀ መጥቶ ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ መገንባት የሚያስችል ዓውድ ፈጥሯል፡፡ የመልክአ ምድር፣ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካዊ አመለካከትና ሌሎች ልዩነቶቻችን የኢትዮጵያ ጌጥ እና ዐቅም እንደኾኑ የጋራ አቋም ወስደናል፡፡
ብዝኃነታችን ውበት እና የካበተ ሥልጣኔያችን ማሳያ፣ ከትናንት እስከ ዛሬ የመቻላችን ምክንያት እንደኾነ በአካታች ሀገራዊ ምክክራችን አረጋግጠናል፤ ታሪኮቻችንም ምሥክሮች ኾነው አሳይተውናል፡፡ የዓለምን ታሪክና ፖለቲካ የለወጠው የዓድዋ ድል፤ የኢትዮጵያን ጂኦ-ፖለቲካዊ ዐቅም ያሳደገዉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያን ስም በዓለም በየዓመቱ በበጎ የሚያስጠራዉ አረንጓዴ ዐሻራ ለብዝኃነታችን ዐቅምነት ሕያዉ ምሥክሮች ናቸው፡፡
ለዚህም ነው ጳጒሜን 4ን የኅብር ቀን ብለን ብዝኃነትን የኢትዮጵያ ጌጥ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ እያከበርን የምንገኘው፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ብዝኃነቶች ሀገር በመኾኗ የብዙ ዐቅሞች ባለቤትም ናት፡፡ የብዝኃነትን ጌጥነት እና ዐቅምነት እርስ በርስ መረዳዳት እና አንዳችን ለሌላችን ጥላ ከለላ በመኾን እንገልጸዋለን፡፡ ዛሬ እነዚህን እውነቶች ለዓለም የምንገልጽበት ድንቅ ቀን ነው፡፡
እንኳን ለጳጉሜን 4 የኅብር ቀን አደረሳችሁ!
ጳጒሜን 04 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: