Search

ከግቢ እስከ ሀገር የሰው-ተኮር ልማት፤ የዜጎችን ሕይወት እና ሰብዓዊ ክብር የመቀየር ጉዞ

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 39

አንድ ሀገር አደገች የሚባለው በሚገነቡት ሕንፃዎች ብዛት ሳይሆን በዜጎቿ የኑሮ ጥራት እና በሰብዓዊ ክብራቸው መከበር ጭምር ነው።

የከተሞች ዕድገት የሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ሞተር መሆኑ ባይካድም ልማቱ የሰውን ልጅ ማዕከል ካላደረገ ግን ትርጉሙን ያጣል።

በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ የተጀመረው እና አሁን ላይ በመላው ሀገራችን የተስፋፋው አዲስ የልማት መስመር የሀብት መጠንን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር እና የኑሮ ጥራት ማስቀደምን መርሑ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ሰው-ተኮር የከተማ ልማት ማለት የከተማን ከባቢ ለሰው ልጅ ሕይወት፣ ደኅንነት እና ሁለንተናዊ ዕድገት ምቹ የማድረግ ጥበብ በመሆኑ ዝቅተኛውን ማኅበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት እና ነባር ጎስቋላ መንደሮችን በመቅረፍ የዜጎችን የመኖር መብት ያረጋግጣል።

ይህ አርቆ ዕሳቤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አዋሬ አካባቢ ከጎረቤቶቻቸው በመጀመር የአቅመ-ደካማ ዜጎችን ደሳሳ ቤቶች በማደስ ወደ ዘመናዊ መኖሪያ መንደርነት ከተቀየረበት በጎ ተግባር ጀምሮ፣ ዛሬ ላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና በመንግሥት እና ሕዝብ ቅንጅት በመላው መዲናችን እና ሀገራችን ባህል ሆኖ ተስፋፍቷል።

የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች ተቋማዊ መሆናቸው የተማሪዎችን ተሳትፎ ያሳደገ ሲሆን፣ የምገባ ማዕከላት እና የማዕድ ማጋራት ባሕል ደግሞ አቅም የሌላቸውን ዜጎች ደግፏል።

በአዲስ አበባ በስፋት የተከናወኑት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር አካባቢያዊ ብክለትን በመቀነስ የአካታች አኗኗር ተምሳሌት ሆነዋል።

35 ሺህ በላይ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው እና የማኅበራዊ ጤና መድኅን መስፋፋቱ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የሕክምና እና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል።

ዓለም አቀፍ የመኖሪያ ስፍራዎች እና የከተሞች ጥናት (UN-Habitat) እንደሚያመላክተው፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ መኖሪያ ቤት ማግኘት የዜጎችን ጭንቀት 30 በመቶ የሚቀንስ ሲሆን፣ በተሻሻለ መኖሪያ እና ጤናማ አካባቢ ውስጥ የሚኖር ዜጋ የምርታማነት አቅሙ እስከ 25 በመቶ ያድጋል።

የኢትዮጵያ የእውነት ዕድገት የሚለካው በሚገነቡት ግዙፍ መሠረተ ልማቶች መጠን ብቻ ሳይሆን በእነዚያ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የዜጎች ሕይወት እና ሰብዓዊ ክብር እንዴት ተቀየረ በሚለውም ጭምር ነው።

በየደረጃው የምንገኝ ዜጎች ባለሀብቶች እና አመራሮች በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ውስጥ የሰው ልጅን ደኅንነት እና ፍላጎት ማዕከል ያደረገውን ይህንን የከፍታ ባሕል አጠናክረን ማስቀጠል ይጠበቅብናል።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: