Search

የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ከዕዳ ወደ ትርፋማነት ያሸጋገረው ቁልፍ ተቋም

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 51

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሲነሱ ወደ አብዛኛው ሰው አእምሮ የሚመጣው ቀርፋፋ አሠራር፣ የዕዳ ጫና እና ኪሳራ ነበር።

እነዚህ ተቋማት በታሪካዊ አደረጃጀታቸው ምክንያት በመንግሥት በጀት ላይ ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ግዙፍ ሀገራዊ ሀብቶችን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ይህንን አመለካከት እና ሥር የሰደደ ብልሽት በመቀየር የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ታሪክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል።

ይህ ሉዓላዊ የሀብት ፈንድ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉ አንጋፋ እና ስትራቴጂያዊ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶችን በሥሩ በማስተዳደር የነበረውን የኪሳራ ታሪክ ወደ ስኬት እየቀየረ ይገኛል።

ተቋሙ ያመጣው ዋነኛ ለውጥ መዋቅራዊ አሠራርን ማዘመን እና ተቋማዊ ነፃነትን ማረጋገጥ ነው።

ቀድሞ በተጓተተ አሠራር እና በዕዳ ይታወቁ የነበሩት ድርጅቶች ዛሬ በዘመናዊ የኮርፖሬት አመራር መዋቅር፣ በፋይናንስ ግልጽነት እና በገበያ ውድድር መርህ እንዲመሩ ተደርጓል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አጋርነትን በመፍጠር እና የውጭ ካፒታልን በመሳብ ረገድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው።

በዚህም ምክንያት ተቋማቱ ከኪሳራ ወጥተው አስተማማኝ የገቢ፣ የግብር እና የሥራ ዕድል ፈጣሪ መሆን ችለዋል፡፡

ይህንን ፈጣን ለውጥ በቅርበት የተመለከቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሳይቀሩ "ከፊስካል ጫና ወደ ኢኮኖሚ ሞተርነት የተሸጋገረ የስኬት ሞዴል" ሲሉ መስክረውለታል።

ከዚህ በተጨማሪ በቁጥር የሚገለጽ ተጨባጭ ውጤትም ተመዝግቧል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚያስተዳድራቸው ተቋማት ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 37.6 ቢሊዮን ብር የትርፍ ድርሻ ወይም ዲቪደንድ ለመንግሥት ገቢ በማድረግ ከፍተኛ ትርፍ አስመዝግበዋል፡፡

እውነተኛ ተቋማዊ ማሻሻያ የሚጀምረው ከውስጥ አሠራርን በመፈተሽ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሕዝብ ንብረት የሆኑ ተቋማትን እሴት በማሳደግ እና በማዘመን የዛሬን ተጨባጭ ውጤት እያጎላ የነገን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ መሠረት እያረጋገጠ ይገኛል።

መልካም አዲስ ዓመት!

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: