በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት ይሠራበት የነበረው እና የተወሰኑ አካባቢዎችን ‘አጋር’ በማለት ከዋናው የውሳኔ ሰጪነት ሚና የማግለል አካሄድ በአካታች የፖለቲካ መዋቅር ተቀይሯል።
በተለይም በ2012 ዓ.ም አዲሱ መዋቅር ሲዘረጋ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ከታዛቢነት ወደ እኩል ባለቤትነት መሸጋገራቸው የዚህ ፖለቲካዊ መታደስ ማሳያ ነው።
ይህ ሽግግር የመዋቅር ለውጥ ብቻ ሳይሆን ልዩነቶችን እንደ ስጋት ማየትን በማስቀረት፣ ብዝኃነትን የጋራ አቅም ያደረገ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው።
የቀደመው የፖለቲካ አስተዳደር ጥቂቶችን ማዕከል፣ ሌሎችን ደግሞ ዳር ላይ ያስቀመጠበት የጥርጣሬ አካሄድ አሁን ላይ አብሮነትን በሚያጸና እሳቤ እየተተካ ይገኛል።
የፖለቲካ ኃይሎችን በጠላትነት የመፈረጅ ልማድ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲመጣ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው።
በመደመር ፍልስፍና የሀሳብ ብዝኃነት ሀብት እንጂ የመለያያ ምክንያት ባለመሆኑ፣ ልዩነቶች በሰለጠነ መንገድ የሚስተናገዱበት ባህል መገንባት ጀምሯል።
በዘመናት ታሪካችን ውስጥ የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፖለቲካ ምህዳሩን ሊያሰፋ የሚችል ትልቅ ሀገራዊ እርምጃ ነው።
የልዩነት ድምፆች የሚሰሙበት ሰፊ የምክክር መድረክ መፈጠሩ፣ የፖለቲካ ኃይሎች የሂደቱ ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ የነገ አቅጣጫ ጠቋሚ እና እውነተኛ ባለድርሻ እንዲሆኑ ዕድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያውያን የቆዩ የማኅበራዊ ትስስር እሴቶች ዛሬ ለዘመናዊው ሰው ተኮር ልማት የጀርባ አጥንት እየሆኑ ነው።
እንደ ዕድር፣ ደቦ እና የጎረቤት መደጋገፍ ያሉ የቆዩ ሕዝባዊ እሴቶችን በማስፋት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ እና የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሮች በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
እነዚህ ተግባራት መንግሥት የሚከተለውን የዜጎች ደኅንነት ፖሊሲ ከሕዝቡ ባህል ጋር ያቆራኙ ህያው ምሰሶዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበት ደረጃ የዜሮ ድምር ፖለቲካን በማስቀረት ብዝኃነት በጌጥነቱ ተከብሮ የጋራ ባለቤትነት የሚረጋገጥበትን መንገድ እየጠረገ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ ያላቸው ተሳትፎ እና ባህላዊ የመረዳዳት እሴቶቻችን ወደ ልማት መለወጣቸው፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በጽኑ አብሮነት ላይ እንድንገነባ አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: