Search

ከፋፋይ ትርክቶችን በመቅበር አብሮነታችንን ያጸናንበት “አንድ ጀምበር”

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 75

ሐምሌ 27 ቀን 2018 . ሀገራችን ታሪክን በአዲስ መልክ የጻፈችበት፣ አይቻልም አስተሳሰብ በኅብረት ክንድ የናደችበት እና ኢትዮጵያውያን ታላቅ የዜግነት ገድል የፈፀሙበት ዕለት ነው።

በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በቋንቋ፣ በባህልና በፖለቲካ እይታ ሳይለያዩ በነቂስ ወጥተው በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በጽኑ ኅብረብሔራዊ አንድነታቸው ዓለምን አስደምመዋል።

በአንድ ጀምበር ከተሞች ከገጠሮች፣ ወጣቶች ከአረጋውያን፣ የተለያየ እምነት ተከታዮችና የብሔር ተወካዮች አንዱ ከሌላው እጅ ለእጅ ተያይዘው ይህን ታላቅ ድል በጋራ ማሳካት ችለዋል።

በዚህ ቀን የተከልነው ችግኞችን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያንን ወንድማማችነት፣ እውነተኛ መተማመን እና ሀገራዊ አብሮነትን ጭምር ነው።

በአንፃሩ በልዩነቶቻችን ላይ በማተኮር ሀገራዊ የጋራ አቅማችንን ለመበተን የተጫኑብን ከፋፋይ ትርክቶች ከተከልናቸው ችግኞች ጋር ለዘለዓለሙ አፈር ውስጥ ተቀብረዋል። በዚህም የወደፊቷን ኢትዮጵያ በገዛ እጃችን የመቅረጽ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።

በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላው ያስመዘገብነው ይህ አስደማሚ ስኬት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሕልም ዙሪያ ስንሰባሰብ የማንሻገረው ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ፈተና እንደሌለ ዳግም ያረጋገጠ ነው።

ይህ የአንድ ጀምበር ክንውን ለዓመታት ሚዘልቅ የሥነ-ምህዳር ውበት ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን የውሃ አካላት ከአፈር መሸርሸር የሚታደግ፣ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድግ እና የምግብ ሉዓላዊነታችንን የሚያረጋግጥ ስትራቴጂያዊ ድል ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከቁጥሮቹ ባሻገር በመሬት ላይ የተከናወነው ይህ ጥልቅ ትርጉም ያለው ሁነት የትውልድ ቅብብሎሽ እውነታ ነው።

በጥቅሉ በሐምሌ 27 ያኖርነው ታሪካዊ ዐሻራ በቁጥርና በቃላት ብቻ የሚገለጽ ባዶ መፈክር ሳይሆን በሁላችንም ላብ የተጻፈ፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጸና እና ሀገራችንን ወደሚመጥናት የከፍታ ማማ የሚያሸጋግር የጋራ ታሪካችን ነው።

በሐና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: