ኢትዮጵያ በብዙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ባህሎች እና እሴቶች የበለጸገች መሆኗ፣ ሕዝቧን ለዘመናት አስተስስረው እና አጽንተው ያቆዩ በርካታ ሀገር በቀል አሠራሮች እንዲኖሯት አስችሏል። ከእነዚህም መካከል የመረዳዳት እና የትብብር ባህል ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል።
በማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ እንደ ደቦ፣ ዕድር፣ ወንፈልና ዕቁብ ያሉ ባህላዊ እሴቶች የዕለት ተዕለት ውሎ መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ የሕዝቡን ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት የሚቃኙ ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።
እነዚህ ጥንታዊ አሠራሮች ዛሬ ላይ ለምናስበው ዘመናዊ የሀገር ግንባታ፣ ለማኅበራዊ አብሮነት እና ለዘላቂ ልማት የሚጫወቱት ሚና እጅግ የጎላ ነው።
በየአካባቢው የተለያየ ስያሜ እና አፈጻጸም ይኑራቸው እንጂ፣ የሁሉም ባህላዊ የመረዳጃ ተቋማት ማዕከላዊ እሴት አብሮነትና ትብብር ነው።
ዕድር በዋናነት በችግርና በሐዘን ጊዜ አባላትን ለመደገፍ የተቋቋመ ማኅበራዊ አወቃቀር ነው። አንድ ቤተሰብ ሐዘን ሲደርስበት አባላቱ የሞራል፣ የጉልበት እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የሐዘኑን ጫና ያቃልላሉ።
በአሁኑ ዘመን ደግሞ እነዚህ ተቋማት ሕጋዊ የሲቪክ ማኅበራት ሰውነት በማግኘት ከመጠያየቅ ባለፈ የጤና ኬላዎችን በማስገንባት፣ አካባቢን በማልማት እና የሕዝብን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ትልቅ ሀገራዊ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ደቦ እና ወንፈል በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እና በከባድ የጉልበት ሥራዎች ላይ የሚታዩ ታላላቅ የትብብር መንገዶች ናቸው። አርሶ አደሮች ጉልበታቸውን እና ሀብታቸውን አስተባብረው በጋራ በመሥራት የሥራ ጫናን እና የጊዜ ብክነትን ይቀርፋሉ።
ይህ ጥንታዊ ትብብር ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እና ለዘመናዊ የግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት መፈጠር ጠንካራ መሠረት ሆኗል።
እንደዚሁም ዕቁብ ያለምንም ቢሮክራሲ እና ወለድ የፋይናንስ አቅምን የሚያሳድግ ጠንካራ ባህላዊ ተቋም ነው።
በመላው ኢትዮጵያ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሰው ዕቁብ፣ አባላቱ በጥቅል የሚሰበስቡትን ገንዘብ በዕጣ በማከፋፈል ለንግድ፣ ለቤት ግንባታ እና ለሌሎች ትላልቅ የኢኮኖሚ ግቦች እንዲበቁ ያደርጋል።
የፋይናንስ ተቋማት ይህን አሠራር ከዘመናዊው የባንክ ሥርዓት ጋር ለማስተሳሰር የሚያደርጉት ጥረት የዚሁ ዘመናዊ ሽግግር ማሳያ ነው።
በመንግሥት ደረጃ የሚሰጡ የማኅበራዊ ዋስትና እና የመድኅን አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ባልተዳረሱባቸው አካባቢዎች እነዚህ ተቋማት በአደጋ ጊዜ የሚደርሱ ዋና የሕዝብ ዋስትና መረቦች ናቸው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ ወይም በጾታ ሳይወሰኑ ሰዎችን በአንድ ማህበራዊ ጥላ ስር በማሰባሰብ ጠንካራ ሀገራዊ መቻቻልን ያሰፍናሉ።
ዕቁብን ከዘመናዊ የፊንቴክ አሠራሮች ጋር በማቀናጀት የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ዕድሮችን ወደ ማኅበረሰብ ጤና ዘመቻዎች መሪነት ማሸጋገር፣ እንዲሁም የደቦን እሴት ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማምጣት የዘመኑ ታላቅ ዕድል ነው።
የመረዳዳት ባህላችን ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ ሀገራዊ ሀብት በመሆኑ፣ እነዚህን አሠራሮች አጠናክሮ ወደ ዘመናዊ የመልካም አስተዳደር ማዕቀፎች ማሸጋገር ለተረጋጋች፣ ለተሳሰረች እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ ግንባታ የማይተካ ሚና አለው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: