Search

የአዲስ አበባ ከተማ አረንጓዴ አብዮት እና የሥነ-ምኅዳር ከፍታ

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 70

ተፈጥሮ ንጹሕ አየርን፣ ዝናብን እና ለምለም መሬትን በመለገስ የሰውን ልጅ ሕልውና ስትደግፍ፣ ሰው ደግሞ እሷን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

ይህንኑ የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅ 2011 . የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ንቅናቄ፣ ዛሬ ላይ የአዲስ አበባን ገጽታ በዘላቂነት እየቀየረ ይገኛል።

በመረጃዎች እንደተረጋገጠው በአዲስ አበባ የደን ሽፋን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከመጀመሩ በፊት ከነበረበት 2.8 በመቶ ብቻ አሁን ላይ ወደ 24 በመቶ ማደግ ችሏል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በመዲናዋ ከተተከሉት 90 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 86.82 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸው የዜጎችን የተቀናጀ ባለቤትነት እና የሥራውን ውጤታማነት የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ አኃዛዊ ዕድገት ለከተማዋ አየር ንብረት መስተካከል እና ለሥነ-ምኅዳር ሚዛን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የጎርፍ ተጋላጭነትን በመቀነስ የላይኛው የአፈር ክፍል እንዳይታጠብ ከመከላከል ባሻገር እንደ ቡና፣ አቮካዶ እና ማንጎ ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መተከላቸው የከተማ ግብርናን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ዕውን እያደረገ ይገኛል።

የመዲናዋ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ከኮሪደር ልማት፣ ከወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እና ከሌማት ትሩፋት ጋር በመቀናጀቱ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ አድርጓታል።

እንደ ቶኪዮ፣ ፓሪስ እና ኒውዮርክ ያሉ ትልልቅ ከተሞች ኮንክሪት የበዛበትን የከተማ ሙቀት ለመቀነስ ቢሊዮን ዶላሮችን በቴክኖሎጂ ላይ ሲያፈሱ አዲስ አበባ ግን በተፈጥሮ ተኮር የመፍትሔ ዕርምጃዎች ፈጣን ለውጥ በማስመዝገብ ለደቡብ ዓለም ከተሞች ድንቅ ሞዴል ሆናለች።

ይህ መርሐ ግብር በየዓመቱ ሲከናወን ለነገው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ የሚከናወን የዘመናችን ዐርበኝነት እና የፈካ የመደመር ትውልድ ዐሻራ ነው።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: