የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት አዲሱን የ2019 አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እርምት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ የቆዩ 676 ታራሚዎችን በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን አስታወቀ።
ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ታራሚዎች መካከል 660ዎቹ ወንዶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 16ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸዉ።
የዚህ ውሳኔ መሠረት የሆነው የክልሉ የይቅርታ ቦርድ፤ ታራሚዎቹ ያቀረቡትን የይቅርታ ጥያቄ ከመንግስት፣ ከህዝብ እና ከታራሚዎች ሁለንተናዊ ጥቅም አንጻር በጥልቀት በመመዘን ቦርዱ የይቅርታ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ መስፈርቱን ያሟሉትን ብቻ በመምረጥ ለክልሉ መንግስት ማቅረቡ ታውቋል።
በማረሚያ ተቋም ቆይታቸው በመልካም ሥነ-ምግባራቸው መታረማቸውን እና መታነፃቸውን ከየደረጃው በሚገኙ የጸጥታና ፍትህ ተቋማት በበቂ ሁኔታ የተረጋገጠላቸው እነዚህ ግለሰቦች፤ ከዚህ በኋላ ለህብረተሰቡ የስጋት ምንጭ ሳይሆኑ ሰላምን የሚሰብኩ፣ አምራችና ህግ አክባሪ ዜጎች በመሆን ማህበረሰቡን እንዲቀላቀሉ የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ መንግስት አያይዞም ህብረተሰቡ ከእስር የተለቀቁትን ዜጎች መታረምና መታነጽ ተገንዝቦ እንዲቀበላቸውና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው አሳስቧል። ይሁን እንጂ ከእስር ከወጡ በኋላ የይቅርታውን ዓላማ በመዘንጋት በድጋሚ ህግን የሚጥሱ አካላት ካጋጠሙ፣ ህብረተሰቡ በተለመደው አጋርነቱ ለፍትህ አካላት ፈጣን ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፏል።
በሰለሞን ባረና
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: