ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት የጉባ ብሥራቶችን በተግባር የምትተረጉምበትና የላቀ ስኬት የምታስመዘግብበት ዘመን እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረጓቸው ሰባቱ የጉባ ብሥራቶች፤ የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ የጋዝ ፋብሪካ ማስመረቅ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እውን ማድረግ፣ በአፍሪካ ግዙፉን አየር ማረፊያ መገንባት፣ 2ኛውን የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመር እና በመላው ሀገሪቱ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን መገንባት ዋና ዋናዎቹ የታቀዱ ግዙፍ ስራዎች ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም፣ በ2019 አዲስ ዓመት የጉባ ብሥራቶችን የበለጠ ተግባራዊ የምናደርግበት ዓመት ይሆናል ብለዋል፡፡
አዲሱ ዓመት የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ የተለያዩ ዕሳቤዎችንና አካሄዶችን በብሔራዊ ጥቅም አስተሳስረን የምንጓዝበት ዓመት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
አዲሱ ዓመት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን የሚከበርበት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን የሚጸናበት፣ የጀመርነው ምርታማነት በዓይነትና በጥራት የሚጨምርበት፣ ሀገራችንም የአፍሪካ መሪነቷን የምታረጋግጥበት እና የብልጽግና ጉዞዋ ትውልድ ተሻጋሪ የሚሆንበት ዘመን እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ግብ እንዲሳካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ፣ የልሂቃን ሚና፣ የሃይማኖት አባቶች ጸሎት፣ የጸጥታ ተቋማት ቁርጠኝነት፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ትጋት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ቅልጥፍና፣ የአርሶ አደሩ አይበገሬነት፣ የወጣቶችና የሴቶች ጥረት፣ የሚዲያዎች ሐቀኝነት፣ የዲጂታል ዘርፉ ዘመናዊነት እንዲሁም የሲቪል ሰርቫንቱ ንጽሕናና አገልግሎት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ሐሳብ፣ አዲስ ታሪክና አዲስ ሥልጣኔ የምንጽፍበት ብሩህ ተስፋ የተሞላበት ዘመን እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: