የአፍሪካን የዕድገት እና የትሥሥር ትርክቶች ከአኅጉሪቱ ዕይታ አንጻር በስፋት የሚያቀርበው ታዋቂው ‘ታይም አፍሪካ’ መጽሔት፣ ሰሞኑን "አፍሪካን የማስተሣሠር ኃይል" በሚል ርዕስ ባወጣው ሐተታ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጠቀሜታ በሰፊው አብራርቷል።
መጽሔቱ የሕዳሴው ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት በዘለለ የነገዋ አፍሪካ የትሥሥር፣ የመተማመን እና የተስፋ ሕያው ምልክት መሆኑን በጥልቀት ተንትኗል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት የነበረውን ታሪካዊ ሕልም ዕውን ያደረገ፣ በጽናት እና በጥብቅ አንድነት የተገነባ የሕዝቦች ኩራት እና የዘመናችን ታላቅ የአፍሪካውያን የስኬት ማሳያ ሆኖ ብቅ ማለቱንም አስምሮበታል።
መጽሔቱ በትንታኔው ትኩረት ከሰጠባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ ግድቡ የፋይናንስ የተደረገበት መንገድ ነው። አፍሪካውያን የገጠማቸውን ሰፊ የመሠረተ ልማት የፋይናንስ ክፍተት እንዴት በራስ አቅም መሙላት እንደሚችሉ ሕዳሴው ግድብ ተግባራዊ ማሳያ እንደሆነ በስፋት ያትታል።
ኢትዮጵያውያን የውጭ ድጋፍን ወይም ብድርን ሳይጠብቁ በውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን በማስተባበር ቦንድ በመግዛት ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ዕውን ማድረጋቸው፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን መሠረተ ልማት በራሳቸው አቅም መገንባት እንደሚችሉ ያረጋገጠ ልዩ "የአፍሪካውያን መፍትሔ" መሆኑን ታይም አፍሪካ ገልጿል።
ይህ ተግባር ሕዝቦች በራሳቸው ልማት ላይ ያላቸውን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያሳይ ታላቅ ትምህርት ነው።
ከውኃ ክፍፍል ይልቅ የጋራ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በሚያነሳው የዘገባው ክፍል፣ አኅጉሪቱ በውዝግብ እና በግጭት ልታድግ እንደማትችል በግልጽ ያመላክታል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረቱን በኢትዮጵያ እና በታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች መካከል በሚነሡ አለመግባባቶች እና ስጋቶች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ግድቡ ያለውን አኅጉራዊ አስተሣሣሪነት እና የትብብር ዕድል ማየት እንዳለባቸው ዘገባው ያሳስባል።
ሳይንሳዊ ጥናቶችን ዋቢ የሚያደርገው ይህ ትንታኔ ኢትዮጵያ ከግድቡ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ገበያዎች ስትሸጥ የኃይል ማመንጫ ሞተሮቿን ለማንቀሳቀስ ውኃውን ወደ ታች ትለቅቃለች።
በመሆኑም ፕሮጀክቱ ግብጽን እና ሱዳንን በቅናሽ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውኃ ፍሰታቸውን በተሻለ ሁኔታ የሚያስተካክል እንጂ ስጋት የሚሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ያስረዳል። ይልቁንም ወንዙን የልዩነት ሳይሆን የትብብር መድረክ ሊያደርጉት እንደሚገባ መክሯል።
ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ ትልቅ አብዮት በመፍጠር ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ለዜጎች የተሻለ ሕይወት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ታይም አፍሪካ መጽሔት በትክክል እንዳስቀመጠው አፍሪካ ያለ በቂ ኤሌክትሪክ ኃይል ማደግም ሆነ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ መሸጋገር አትችልም። የኤሌክትሪክ መስመሮች ደግሞ በድንበር የሚገደቡ አይደሉም።
ስለሆነም ግድቡ ቀጣናዊ የኃይል ገበያን በማስተሣሠር የምሥራቅ አፍሪካን ምጣኔ ሀብት በጋራ ለማሳደግ እና አስተማማኝ የመሠረተ ልማት ሽግግር ለማምጣት እንደ ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የራሷን የልማት መብት እያረጋገጠች የሌሎችንም ጥቅም ያከበረችበት የአፍሪካውያን የዲፕሎማሲ ብስለት ማሳያ ነው።
መጽሔቱ አበክሮ እንደገለጸው፣ ሉዓላዊነት እና አኅጉራዊ አንድነት የሚጣረሱ ሐሳቦች አለመሆናቸውን የአፍሪካ ኅብረት መርሆዎች ያሳያሉ፤ የሕዳሴው ግድብ ደግሞ ይህንን መርሕ በተግባር ያረጋገጠ ሕያው ምሥክር ነው።
ይህ ፕሮጀክት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የትብብራችን ፍሬ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ትሥሥር ያበረከተችው ታላቅ ስጦታ ነው።
ሕዳሴ የውኃ ፖለቲካን ወደ መተማመን እና ወደ ጋራ ብልጽግና የቀየረ የአፍሪካውያን የጋራ ድል ነው!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: