Search

"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቀይ መስመራችን ነው"፦ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ዓርብ መስከረም 01, 2019 118

አዲስ የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 2019 . አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና እና የዕድገት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፣ አዲሱ ዓመት ለአዲሱ የምክር ቤት አባላት የተስፋ እና የአዲስ ጅማሮ ምዕራፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የሀገርን ችግሮች በመፍታት፣ ሕግ በማውጣት፣ ፖሊሲ በመቅረጽ እና ተቋማትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የቀጣዮቹ 5 ዓመታት የሥራ ዘመን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ገንቢ በሆነ ውይይት እና በሀገራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የሰላም እጦት ችግር ለመፍታት፣ የምክር ቤት አባላት ከየትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በላይ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነት እና ሉዓላዊነት በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የሐሳብ ልዩነት መኖሩ ጤናማ ቢሆንም፣ እነዚህ ልዩነቶች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ መሆን እንደሌለባቸው እና "ቀይ መስመር" ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። በምክር ቤቱ ውስጥ ከማንጓጠጥ እና ከመቃቃር ይልቅ፣ የፖለቲካ ባሕልን ወደ ገንቢ የሐሳብ ውይይት መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ ለዓለም ያቀረበችው የባሕር በር ጥያቄ በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ ዕውን እንዲሆን እንዲሁም በምክር ቤቱ ለሕዝብ ጥቅም በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በምርጫው ማግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተወካዮች በአክብሮት እና በፍቅር የመቀበል እንዲሁም አብሮ የመሥራት ባሕል እያዳበሩ መሆናቸውን እንደ በጎ ጅምር ጠቅሰዋል።

በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: