የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዳግም መቋቋሙን ተከትሎ ብሔራዊ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የሰው ኃይልን በዘመናዊ ሥልጠና የመገንባት፣ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮችን የመዘርጋት እና የብሔራዊ ደኅንነት ሥራዎችን በላቀ ደረጃ እያከናወነ ይገኛል።
በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እና ዓለም አቀፋዊ የባሕር ላይ ንግድ መስመሮችን ደኅንነት ግምት ውስጥ ያስገባው ይህ የአቅም ግንባታ ሥራ፣ በዘርፉ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኃይል ለመፍጠር ያለመ ነው።
የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ እንደገለጹት ተቋሙ በሙሉ አቅሙ እና በራሱ ብቃት የመሠረታዊ ባሕርተኞችን እና የበታች ሹሞችን ሥልጠና በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በአዲስ አበባ የተገነባው የባሕር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ የቢሾፍቱ መሠረታዊ ማሠልጠኛ ማዕከልም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በባሕር ዳር ዙሪያ የሚገኘው የባሕር ኃይል ካዴት አካዳሚ በቅርብ ቀናት በይፋ የሚከፈት ሲሆን፣ ይህም ለቀጣዩ ትውልድ ወታደራዊ ማሪታይም መሪዎች ማፍሪያ ዋና ማዕከል ይሆናል።
የባሕር ኃይል አካዳሚ አዛዥ ካፒቴን ከበደ ሚካኤል በበኩላቸው፣ ወጣት ባሕርተኞች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና የማሪን ኮማንዶ አባላት በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሠለጠኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሠልጣኞቹ ከማሪን ኮማንዶ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ብሔራዊ የውኃ አካላትን ጥበቃ፣ የቅኝት እና የጸጥታ ማስከበር ሥራዎችን በቀንም ሆነ በምሽት በ24 ሰዓት ሙሉ ዝግጅት በብቃት እያከናወኑ ይገኛል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን እና ብሔራዊ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ ወደ ቀይ ባሕር፣ ባሕረ ሰላጤው እና ሕንድ ውቅያኖስ ለመውጣት ጥረት የህልውና ጉዳይ እንጂ የትርፍ ጊዜ ምርጫ አይደለም።
የቀይ ባሕር እና የባብ ኤል-ማንዳብ ቀጣና የዓለም አቀፍ ንግድ ዋና ማዕከል በመሆኑ፣ በዚሁ ቀጣና ሰላም እና ደኅንነትን ማስከበር ለኢትዮጵያም ሆነ ቀጣናው ለሚገኙ ሀገራት ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሠረት ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሀገር ውስጥ የውኃ አካላትን ከሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ከመጠበቅ ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ውኃዎች ላይ አዎንታዊ የማሪታይም ድርሻውን የሚወጣበት እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብርበት ጊዜ እጅግ እየቀረበ ይገኛል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: