ዓለማችን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አይታው ወደማታውቀው የባለብዙ ዋልታ የሽግግር ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች።
በዚህ ታሪካዊ ዘመን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከዕርዳታ እና ከብድር ጥገኝነት ወጥቶ እንዲሁም ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነት ተሸጋግሯል።
ኢትዮጵያ የዓለምን 49 በመቶ ሕዝብ እና 40 በመቶ ጠቅላላ ኢኮኖሚ የሚወክለውን የብሪክስ (BRICS) ስብስብ ሙሉ አባል መሆኗ የዚህ የልዕልና ጉዞ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
የብሪክስ አባልነት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ተሰሚነት እና የዲፕሎማሲ አካሄድ ውጤት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ ባለው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ከሕንድ፣ ሩሲያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ማሌዢያ፣ ኢራን እና ከካዛኪስታን መሪዎች ጋር ያደረጉት ሁለገብ ውይይት የዚህ ማሳያ ነው።
ውይይቶቹ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ ማዕድን ልማትን፣ ኢንቨስትመንትን እና በተለይም የቀይ ባሕርን ደኅንነት ያማከሉ መሆናቸው ዲፕሎማሲያችን ምን ያህል ስትራቴጂያዊ እና ቀዳሚ ዕርምጃ ወሳጅ እንደሆነ ያመላክታሉ።
ከምዕራቡም ሆነ ከምሥራቁ ዓለም ጋር የጥቅም ሚዛንን የጠበቀ ግንኙነት መመሥረቱ በማንም ወገን ሳንጠለል ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተዘረጋ የተመጣጠነ ፖሊሲ ነው።
ይህ አዲሱ የዲፕሎማሲ ከፍታ የተገነባው በኃይል ማስገደድ ሳይሆን "ልዝብ ኃይል" (Soft Power) በሚባለው የማሳመን ጥበብ ነው።
ዘመናዊው የኮሪደር ልማት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝነታችን እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ ያደረጉ አየር መንገዳችን እና አትሌቶቻችን ኢትዮጵያን ለቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጓት ነው።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይል እና በመሠረተ-ልማት የተዘረጋው ትሥሥር እንዲሁም የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት፣ የዚሁ ብሔራዊ ልዕልናን የማረጋገጥ አካል ነው።
ሆኖም ይህ እጅግ ተስፋ ሰጪ የሆነ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ስኬት ዘላቂ እንዲሆን የሀገር ውስጥ የሰላም ግንባታን እና የተጀመረውን ሀገራዊ መግባባትን ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን ማረጋገጥ አለብን። ጠንካራ እና የተረጋጋች ሀገር ለዲፕሎማሲ ስኬት ዋስትና ናት እና።
እንዲሁም በብሪክስ አባልነት የተከፈቱትን ሰፊ የገበያ እና የፋይናንስ አማራጮች ወደ ተግባር ለመቀየር፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የበለጠ ማዘመን እና የሎጂስቲክስ አቅማችንን ማሳደግ የግድ ይለናል። የተገኙት የዲፕሎማሲ ድሎችም በጥናት እና ምርምር ላይ በተመሠረተ ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር ውስጥ ሊዋሐዱ ይገባል።
በተጨማሪም የባሕር በር የማግኘት ጥረታችን የቀጣናው የጋራ ብልጽግና ማሳለጫ እንጂ የጸጥታ ስጋት አለመሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይበልጥ እንዲገነዘበው ስልታዊ የማግባባት ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል።
ኢትዮጵያ የጥገኝነትን አዙሪት ሰብራ ዜጋ ተኮር እና የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ ስትራቴጂ የዓለምን መድረክ በክብር መቀላቀሏ በተግባር ተገልጿል። አሁን የሚጠበቅብን ይህንን የልዕልና ጉዞ በመደመር ዕሳቤ፣ በአንድነት እና በከፍተኛ የሥራ ባህል ከዳር ማድረስ ነው።
ዛሬ የምንጽፈው የዲፕሎማሲ ጥበብ፣ ነገ ልጆቻችን በኩራት የሚያነቡት የኢትዮጵያ የማይናወጥ ከፍታ ይሆናል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: