Search

የኢትዮጵያ እምቅ አቅም እና የብሪክስ የኢኮኖሚ ትስስር

እሑድ መስከረም 03, 2019 114

ኅብር፤ አንድነትን፣ ትብብርን እና ጥምረትን መሠረት በማድረግ ግዙፍ አቅም የሚፈጠርበት መርህ ነው።

ይህ የኅብር እሳቤ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ ሲተረጎም ሀገር በቀል አቅሞችን ከዓለም አቀፍ የካፒታል እና የቴክኖሎጂ አጋርነት ጋር ማስተሳሰርን ያመለክታል።

በተለይም ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ካላቸው ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት አንጻር ሲታይ ሀብትን ከማውጣት ባለፈ በእሴት ጭማሪ ወደላቀ ምዕራፍ መሸጋገር የህልውና ያህል ወሳኝ ጉዳይ ነው።

አፍሪካ በማዕድናት በታዳሽ ኃይል ምንጮች፣ በሰፊ የእርሻ መሬት እና በወጣት የሰው ኃይል የበለጸገች አህጉር ብትሆንም ሀብቷን ወደ ኢንዱስትሪ ምርት እና የሥራ ዕድል የመቀየሩ ጉዳይ ዋነኛ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

አብዛኛው የማዕድን እና የግብርና ሀብት በጥሬ ዕቃነት ወጥቶ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ተቀናብሮ በከፍተኛ ዋጋ ወደ ዓለም ገበያ ይመለሳል።

ይህ የእሴት ሰንሰለት ክፍተት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ግድ ይላል። አሁን ላይ ዋነኛው የኢኮኖሚ ጥያቄ ሀብትን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ተወዳዳሪ የውጭ ገበያ ምርትነት መቀየር ላይ ያተኮረ ነው።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሙሉ አባል ከሆነችበት የብሪክስ (BRICS) ጥምረት ጋር ሲዋሃድ አዲስ የኢኮኖሚ አድማስ ይከፍታል።

የብሪክስ ዋነኛ ዓላማም አባል ሀገራቱ በቴክኖሎጂ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ተደጋግፈው የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው።

እየተካሄደ ያለው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤም በኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል እና በማምረቻ ዘርፎች ላይ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ይህንኑ የደቡብ ለደቡብ የትብብር መንፈስ እና የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያጠናክሩ ናቸው።

የዚህ ትብብር ስኬት መመዘን ያለበትም በጥሬ ዕቃ ሽያጭ መጠን ብቻ ሳይሆን በሚፈጠረው የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሚያሠለጥነው የሰው ኃይል እና በሚከፍተው ሰፊ የኤክስፖርት ገበያ ነው።

በተለይም ቁጥሩ እያደገ ለመጣው ወጣት ትውልድ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው የኢኮኖሚው ማዕከል ከጥሬ ሀብት ላኪነት ወደ እሴት አምራችነት ሲሸጋገር ብቻ ነው።

ማዕድን ማውጣት ውስን የሥራ ዕድል ቢኖረውም ምርቱን ማቀነባበር፣ ማሸግ እና ለገበያ ማቅረብ የሚፈጥረው የሥራ ሰንሰለት እጅግ ሰፊ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለማዕድን፣ ለግብርና እና ለታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ አቅም በማቀናጀት ከብሪክስ የኢኮኖሚ ምኅዳር ጋር መፍጠር ያለባት ኅብር የነገ ብልጽግናዋ መሰረት ነው።

ትልቁ ጥያቄ አፍሪካ ምን ሀብት አላት የሚለው ሳይሆን ያላትን ሀብት ምን ያህል እሴት ወዳለው ምርት መቀየር ትችላለች የሚለው ነው።

ከተፈጥሮ ሀብት ወደ ምርት፣ ከምርት ወደ እሴት፣ ከእሴት ወደ ሰፊ የሥራ ዕድል እና ወደ ውጭ ገበያ የሚደረገው ጉዞ ትክክለኛው የብሪክስ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳያ ነው።

ጥምረቱ የሚያስተምረንም ይህንኑ የተበታተነ አቅምን አሰባስቦ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ወደ ላቀ የብልጽግና ደረጃ መሸጋገርን ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: