Search

የኢትዮጵያ የተግባር ልዕልና በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ

እሑድ መስከረም 03, 2019 143

አንዳንድ የዓለም መድረኮች የተሳትፎ ብቻ ሳይሆኑ የአቅም፣ የዕይታ እና የወደፊት ራዕይ መፈተኛ ናቸው።

በኒው ዴልሂ እየተካሄደ ያለው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤም ከእነዚህ ታላላቅ መድረኮች አንዱ ነው።

በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የራሷን ልምድ፣ የአፍሪካን ፍላጎት እና የዓለም የጋራ ተግዳሮቶችን በማስተሳሰር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አማካኝነት ጠንካራ አቋሟን አንጸባርቃለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከውጭ አስመጪነት በመውጣት ማምረት እና ማቅረብ የምትችል ሀገር መሆን መጀመሯን አስምረውበታል።

በምግብ ራስን መቻል፣ በጤና፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዘርፍ አፍሪካ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን በምርምር እና ቴክኖሎጂ የምትሳተፍ አህጉር መሆን እንዳለባት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከብሪክስ አባል ሀገራት ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ከብሪክስ የካፒታል እና ቴክኖሎጂ አቅም ጋር በማጣመር ማዕድን፣ ታዳሽ ኃይል እና የኢንዱስትሪ ዘርፎችን የኢኮኖሚ ትብብሩ ዋነኛ ምሰሶዎች ለማድረግ ያላትን ዝግጁነት በግልጽ አሳይታለች።

በአረንጓዴ ልማት ዘርፍም የተገኘው ስኬታማ ልምድ ለመድረኩ ቀርቧል። የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ልማት ሥራዎች ከብልጽግና ጉዞ ጋር በጥብቅ የተያያዙ መሆናቸው ተብራርቷል።

ኢትዮጵያ 2027 የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ ያላትን ዝግጅት መግለጿ በዓለም የአየር ንብረት አጀንዳ ውስጥ ድምጿን ከፍ ለማድረግ ያላትን ጽኑ ፍላጎት በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።

በዚህ ሁሉ ሂደት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር ዕይታ ይበልጥ ጎልቶ ወጥቷል። ዲፕሎማሲን ከፖለቲካዊ ግንኙነት በላይ በማሸጋገር ከምግብ ዋስትና፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ ታዳሽ ኃይል እና ንግድ ጋር ማስተሳሰር የዘመናዊው የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መገለጫ ሆኗል።

የኒው ዴልሂው መድረክ ኢትዮጵያ ለመጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለማበርከት፣ እንዲሁም ተቀባይ ብቻ ሳትሆን አጋር ለመሆን መቁረጧን ያረጋገጠ ነው።

ተመልካች ሳትሆን በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ድምፅ ለማሰማት በተግባር እየተንቀሳቀሰች ስለሆነ፤ ከታላላቆቹ የዓለም ሀገራት ጋር በኩራት መቆም የሚገባት በታሪኳ ብቻ ሳይሆን በዛሬው ተጨባጭ አቅሟና በነገው ብሩህ ራዕይዋ ጭምር ነው።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: