Search

የብሪክስ አባል ሀገራት የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት፣ የ'ICAO' ዕጩነትን እና የ'COP32' አዘጋጅነትን በጽኑ ደገፉ

እሑድ መስከረም 03, 2019 148

በሕንድ ኒው ዴልሂ ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው 18ኛው የብሪክስ (BRICS) የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈበትን ሰፊ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

140 አንቀጾችን የያዘው የብሪክስ የኒው ዴልሂ የአቋም መግለጫ (BRICS New Delhi Declaration) የዓለም አቀፍ አስተዳደር ማሻሻያ፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ሰላም፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን ያካተቱ አንኳር ጉዳዮች ላይ የጥምረቱን አቋም ያንጸባረቀ ነው።

በተለይም ለኢትዮጵያ ጉልህ ትርጉም ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጥምረቱ ጠንካራ ድጋፉን ሰጥቷል።

በመግለጫው አንቀጽ 20 ላይ፣ አዳጊ ሀገራት ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ለመቀላቀል ያላቸውን ፍላጎት በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ እና ኢራን የዓለም ንግድ ድርጅትን (WTO) ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ጥረት የብሪክስ አባል ሀገራት በጽኑ እንደሚደግፉ ተገልጿል።

በተጨማሪም በመግለጫው አንቀጽ 105 ላይ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ብቸኛ ዕጩ በመሆን በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የቀረበውን ሐሳብ ብሪክስ በደስታ ተቀብሎታል።

በተመሳሳይ በአንቀጽ 107 ላይ፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ፕሬዚዳንትነትን እንድትይዝ ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ አረጋግጠዋል።

ከእነዚህ በተጨማሪ መግለጫው ያካተታቸው ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

ዓለም አቀፍ አስተዳደር እና የባለብዙ ወገን ሥርዓት ማሻሻያ

መሪዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ የፀጥታው ምክር ቤትን እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን (እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ) አሠራር ፍትሐዊ እና አካታች እንዲሆን ጠይቀዋል።

የአፍሪካን፣ የእስያን እና ላቲን የአሜሪካን ጨምሮ አዳጊ ሀገራት በውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ያላቸው ውክልና እንዲያድግ ያላቸውን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የኢኮኖሚ ትብብር፣ ንግድ እና ፋይናንስ

አባል ሀገራቱ ድንበር ዘለል የክፍያ ሥርዓቶችን በማቀላጠፍ የንግድ ልውውጥን በሀገር ውስጥ ገንዘቦች ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

አዲሱ የልማት ባንክ (NDB) አዳጊ ሀገራት የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ አቅርቦት በመደገፍ ረገድ የሚጫወተውን ሚና አድንቀው፣ የባንኩን አባልነት ለማስፋፋት ተስማምተዋል። ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጭ የሚጣሉ የተናጠል የኢኮኖሚ ማዕቀቦችንም በጥብቅ አውግዘዋል።

ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት

ጉባኤው በዓለም ዙሪያ የሚታዩ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እና በዲፕሎማሲ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። በጋዛ፣ ሊባኖስ፣ ሱዳን፣ እና ሶሪያ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲረጋገጥ የጠየቀ ሲሆን፤ በተለይ በሱዳን ላለው ቀውስ "የአፍሪካ መፍትሔ ለአፍሪካ ችግሮች" የሚለው መርሕ መሠረት ሊሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥቷል።

የመሪዎች ጉባኤው፣ ሕንድ 2026ቱን የብሪክስ ሊቀመንበርነት እና 18ኛውን ጉባኤ በስኬት በማስተናገዷ ምስጋና በማቅረብ፤ ቻይና 2027ቱን የብሪክስ ሊቀመንበርነት ተረክባ 19ኛውን የመሪዎች ጉባኤ እንድታስተናግድ ሙሉ ድጋፉን ሰጥቷል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: