Search

የብሪክስ መሪዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጠቃላይ ሪፎርም እንዲደረግበት ጠየቁ

እሑድ መስከረም 03, 2019 153

በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ ባለው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ እና ውክልናን ያረጋገጡ እንዲሆኑ አጠቃላይ የማሻሻያ (ሪፎርም) ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠየቀ።

ከዚህ ቀደም ተመድ እና የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም እንዲደረግባቸው እና አፍሪካ ተገቢውን ውክልና እንድታገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) መጠየቃቸው አይዘነጋም።

የብሪክስ መሪዎች ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ ላይ፣ በተለይም አሁን ያለውን የዓለም አቀፍ ግንኙነት መዋቅር የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታዎች ይበልጥ እንዲያንጸባርቅ አድርጎ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።

መግለጫው በተለየ ሁኔታ አሁን እየተካሄደ ያለውን የቀጣዩን የተመድ ዋና ጸሐፊ ምርጫ ሒደት በማንሣት፣ በድርጅቱ ታሪክ እስካሁን ድረስ አንዲትም ሴት ለዋና ጸሐፊነት ተመርጣ እንደማታውቅ በትኩረት አንሥቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ከላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን አንድ ሰው ብቻ፣ ከአፍሪካ እና ከእስያ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሁለት ሰዎች ብቻ ይህንን ቦታ መያዛቸውን በማስታወስ የውክልና ክፍተቱን አመላክቷል።

የተመድን የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርምን በተመለከተም መሪዎቹ ጠንካራ አቋም አንፀባርቀዋል። ምክር ቤቱ አሁን ላለው ዓለም አቀፍ ፈተና ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲችል የአዳጊ ሀገራትን ውክልና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ እና በተለይም በአፍሪካ ሀገራት ኤዙልዊኒ ስምምነትእና ሲርቴ የአቋም መግለጫላይ የተንጸባረቀው ሕጋዊ ጥያቄ ዕውቅና ሊኖረው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም የደቡቡን ክፍለ ዓለም ድምፅ እንዲጎላ የሚያደርግ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት የሆኑት ቻይና እና ሩሲያ፣ ብራዚል እና ሕንድ በተመድ ውስጥ የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ያላቸውን ድጋፍ ዳግም አረጋግጠዋል።

በተመድ ሴክሬታሪያት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ላይ አፍሪካን፣ እስያን እና ላቲን አሜሪካን ጨምሮ አዳጊ ሀገራት ፍትሐዊ የጂኦግራፊያዊ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ የብሪክስ መሪዎች አሳስበዋል።

በእነዚህ ተቋማት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሴቶችን በተለይም ከአዳጊ ሀገራት የመጡ ሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የተመድ የሥራ አስፈጻሚዎች እና የከፍተኛ ኃላፊዎች ሹመት የትኛውንም ሀገር ወይም የሀገራት ስብስብ የበላይነት የሌለበት እና ግልጽነትን የተከተለ መሆን እንዳለበት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።

መሪዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላላ ጉባኤውን ለማነቃቃት፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ምክር ቤቱን (ECOSOC) ለማጠናከር እና የሰላም ግንባታ መዋቅሩን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ሆን ብሎ የገንዘብ መዋጮን በመከልከል የዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ተቋማትን ሥራ ለማዳከም የሚደረጉ የተናጠል ሙከራዎችን አጥብቀው አውግዘዋል።

በዮናስ በድሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: