የአውሮፓ ኅብረት እና አባል ሀገራት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና አካታች ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ገለጹ።
አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ አስደናቂ ውጤት አስመዝግባለች።
መንግሥት የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፣ ትግበራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ንግድ በማስፋት አኅጉራዊ አቅማቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
ጠንካራ የኢኮኖሚ ትሥሥር መፍጠር ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ኅብረት እና አባል ሀገራቱ ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች ስኬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በኃይል፣ በጤና እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፎች የላቀ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ የአኅጉሪቱ የዲፕሎማሲ፣ የትብብር እና የፖሊሲ ዋና ማዕከል መሆኗን ጠቅሰው፣ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዋንም አንሥተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት እና ኢትዮጵያ በጠንካራ እና አስተማማኝ አጋርነት ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ለዚህም ኅብረቱ እና አባል ሀገራቱ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: