የዓለም አቀፍ የንግድ እና የኃይል አቅርቦት ደም ሥር በሆነው በቀይ ባሕር ቀጣና አሁን ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ወታደራዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች የቀጣናውን ሰላም አደጋ ላይ ጥለውታል።
ታሪካዊ እና ጂኦግራፊያዊ ትሥሥር ያላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና መዳረሻ ማግኘቷ ይህን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ወሳኝ መፍትሔ ነው።
የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ መገኘት ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናው ደኅንነት የማይተካ ሚና ይጫወታል።
ለዚህም ግዙፍ የሰው ኃይሏ፣ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ያረጋገጠችው ጠንካራ ወታደራዊ አቅሟ እንዲሁም በተለያዩ አጎራባች ቀጣናዎች በገነባችው የሰላም አስከባሪነት ታሪኳ በተጨባጭ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው።
ኢትዮጵያን ያገለለ የቀይ ባሕር ደኅንነት አወቃቀር ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል የአሁኑ የቀጣናው ምስቅልቅል በግልጽ እያሳየ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በየመን የሚንቀሳቀሰው የሁቲ ቡድን በወሰዳቸው ወታደራዊ እርምጃዎች በባብ ኤል መንደብ ሰርጥ እና በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፉ የንግድ መርከቦችን ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሏል።
የቡድኑ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ያወከ ሲሆን፣ በርካታ ግዙፍ የትራንስፖርት ኩባንያዎች አቅጣጫቸውን ወደ ደቡብ አፍሪካ ‘ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ’ እንዲቀይሩ አስገድዷል።
ይህ ክስተት የመርከብ ትራንስፖርት እና የኢንሹራንስ ወጪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማናር በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ እና የኃይል አቅርቦት ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል።
ምዕራባውያን ኃይሎች የባሕር ላይ ንግዱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ ቢሆንም፣ የቡድኑን ያልተመጣጠነ የውጊያ ስልት በዘላቂነት ማስቆም አልቻሉም።
የቀይ ባሕር ባለቤት ነን ባይ ወገኖች ያቋቋሟቸው የቀጣናው የደኅንነት መድረኮችም አደጋው በደጃቸው ሲያንኳኳ ምንም ዓይነት የመከላከል አቅምም ሆነ ፍላጎት ሳያሳዩ ቆመው እየተመለከቱ ነው።
ይህ ክስተት ኢትዮጵያን ያገለለ የደኅንነት መዋቅር ምን ያህል ደካማ እና ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑን በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ እያንዣበበ ያለውን ስጋት ቀድማ በመረዳት የተለየ ስትራቴጂያዊ ዕይታ ስታራምድ ቆይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና በተለያዩ መድረኮች ባደረጓቸው ማብራሪያዎች ይህንን እውነታ በግልጽ አስምረውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር ተያያዥ እና የማይነጣጠሉ አካላት መሆናቸውን አብራርተው፣ የባሕር መዳረሻ ጥያቄያችን ለቀጣናው ደኅንነት እና ለጋራ ተጠቃሚነት እንጂ በማንም ላይ አደጋ ለመጣል እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የምትፈልገው የባሕር በር መዳረሻ በጦርነት ወይም በኃይል ሳይሆን በዲፕሎማሲ፣ በንግድ ሕግ እንዲሁም በጋራ ብልጽግና መርሕ በሰላማዊ መንገድ የሚፈታ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀዋል።
ፍትሐዊነት፣ ሰላማዊ ድርድር እና ሚዛናዊ የሀብት ክፍፍል የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መሠረታዊ ምሰሶዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚታየውን ሽብርተኝነት፣ የባሕር ላይ ውንብድና እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በመዋጋት ረገድ ተፈትኖ የተረጋገጠ አቅም አላት።
በቅርቡ በናይሮቢ በተካሄደው የቀጣናው የባሕር ላይ ሕግ ማስከበር ውይይት ላይም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የባሕር ላይ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት አስመስክራለች።
ይህን ታሪካዊ እና ቀጣናዊ ኃላፊነት ለመወጣትም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደ አዲስ የተገነባው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በተቋማዊ ብቃት ራሱን በከፍተኛ ደረጃ አዘጋጅቷል።
ይህ ተቋም ወደ ኢትዮጵያ የሚቃጡ ስጋቶችን ከመመከት ባሻገር፣ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ያለውን የባሕር ላይ ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስተማማኝ የደኅንነት አጋር ለመሆን ሙሉ ዝግጁነት አለው።
የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መዳረሻ ጥያቄ የራሷ ሕልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ እየተተራመሰ ላለው የቀይ ባሕር ቀጣና አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና ጭምር ነው።
በቀጣናው ጠንካራ ጦር፣ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር እና የዳበረ የሰላም ማስከበር ልምድ ያላት ኢትዮጵያ ከባሕሩ ርቃ እየተከናወኑ ያሉ የደኅንነት ማስጠበቅ ሥራዎች ውጤት ማምጣት አለመቻላቸውን በተግባር አይተናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳስገነዘቡት የጋራ ጸጋን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መጋራት ሰላምን ያጸናል፤ ተፈጥሯዊ ትሥሥርን መካድ ግን ውሎ አድሮ ቀውሶችን ይወልዳል። አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።
በመሆኑም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ጥያቄ ማስተናገድ በቀጣናው የሚከሰቱ የደኅንነት አደጋዎችን በጋራ ለመቋቋም የሚረዳ እና ለቀይ ባሕር ዘላቂ ሰላም ብቸኛው እና ወሳኙ መፍትሔ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ሕልውና ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ትስስር ዋስትና ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: