የኢትዮጵያ ታሪክ የፈተና ብቻ ሳይሆን፤ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር የተገነባ የትጋት እና የተስፋ ጉዞ ነው።
በተለያዩ ዘመናት የተጋረጡ የውጭ ጫናዎች፣ የውስጥ ችግሮች፣ ጦርነቶች፣ ድርቆች እና ማኅበራዊ ውጣ ውረዶች ሀገራችንን ቢፈትኗትም፤ በሕዝቦቿ ጽናት እና ትግል እስከ ዛሬ በክብር ዘልቃለች።
ይህ ታሪኳ ከውድቀት በኋላ መነሳት፣ ከችግር ውስጥ አቅም መፍጠር እና ከአስቸጋሪ ሁኔታ የተሻለ ሥርዓት መገንባት መቻሏን በጉልህ ያሳያል።
ያለፈውን ታሪክ መዘከር የሚኖረው ትልቁ ዋጋም ከዚህ ይመነጫል። ታሪክ የትናንት ትዝታ ብቻ ሳይሆን፤ የዛሬ ውሳኔን እና የነገ አቅጣጫን የሚያሳይ ብሩህ መስታወት ነው።
ከቀደሙት ፈተናዎች ትምህርት መውሰድ፣ ያለፉ ስህተቶች እንዳይደገሙ መጠንቀቅ እና ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን በውይይት መፍታት ለተሻለ የወደፊት ሀገራዊ ግንባታ ጽኑ መሠረት ይሆናል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በስኬት ያካሄደችው ያለው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ያለፉ ስብራቶችን ለመጠገን እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ዓይነተኛ ማሳያ ነው።
የአንድ ሀገር ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ፈተናዎች ባለመኖራቸው ሳይሆን እነዚህን ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር አቅሟ ነው።
ፈተና እንደ ግድግዳ ከታየ ያቆማል፤ እንደ መወጣጫ ደረጃ ከታየ ደግሞ ወደ ተሻለ ከፍታ ያወጣል። የሚያስፈልገንም ከችግር መሸሽ ሳይሆን ችግሩን ተረድቶ ዘላቂ መፍትሔ የመፍጠር አቅምን ማጎልበት ነው።
ይህ አዎንታዊ አስተሳሰብ በዛሬው የልማት ጉዞአችንም በተግባር እየታየ ይገኛል። የኮሪደር ልማት ትሩፋቶች፣ የከተሞች መሠረተ ልማት መስፋፋት፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የታዳሽ ኃይል ልማቶች፣ ኢትዮጵያን በምግብ ራስን እንድትችል እያደረገ ያለው የግብርና ሽግግር፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እና በቅርቡ የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዛሬን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የሚደረጉ ሳይሆኑ ነገን የሚያዘጋጁ ዐቢይ ክንውኖች ናቸው።
ከዚህም ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረክ የብሪክስ አባልነትን የመሳሰሉ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢኮኖሚ አድማሳችንን እያሰፉት ይገኛሉ።
እነዚህ ሁሉ የነገዋን ኢትዮጵያ በጸና መሠረት ላይ ለመገንባት ዛሬ የሚደረጉ የረጅም ጊዜ ዝግጅቶች ናቸው።
የዛሬው ዘርፈ ብዙ ጥረት የነገ ዕድል፣ የዛሬው ሀገራዊ ኢንቨስትመንት የነገ አቅም እንዲሁም የዛሬው ደፋር ውሳኔ የቀጣዩ ትውልድ የኑሮ መሠረት ይሆናል።
ይህ ሀገራዊ ልማት የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት ነው። ወጣቱ በዕውቀቱ እና በፈጠራው፣ አርሶ አደሩ በምርቱ፣ ሠራተኛው በትጋቱ፣ ባለሀብቱ በኢንቨስትመንቱ እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ በየድርሻው ለሀገር ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የለውጡ ዋና ሞተር ነው።
አዲሱ ዓመት ይህን አዲስ አስተሳሰብ እና ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል ልዩ ዕድል ይሰጠናል። የዓመት መለወጥ የቀን እና የቁጥር መቀየር ብቻ ሳይሆን ያለፈውን በመገምገም ከስኬቶቻችን የምንማርበት፣ ከድክመቶቻችን የምንታረምበት እና የሚገጥሙንን ፈተናዎች ወደ አዲስ ዕድሎች ለመቀየር በጋራ የምንወስንበት ወቅት ነው።
የቀደሙት ትውልዶች የራሳቸውን ታሪክ ጽፈው አስረክበውናል፤ የእኛ ትውልድ ደግሞ የሚቀጥለውን የብልጽግና ታሪክ የሚጽፍበት ጊዜ አሁን ነው።
ይህ ታሪክ በችግር ብቻ ሳይሆን በመፍትሔ፣ በግጭት ብቻ ሳይሆን በውይይት፣ በጥገኝነት ብቻ ሳይሆን በራስ አቅም በመቆም፣ በፈተና ብቻ ሳይሆን በዕድል የሚገለጽ ብሩህ ታሪክ መሆን አለበት።
ልዩነቶቻችንን እያከበርን በጋራ ብሔራዊ ጥቅማችን ላይ መቆም፣ በትጋት እና በፈጠራ መሥራት ከቻልን ዛሬ የሚመስሉንን ፈተናዎች የነገ የልማት መሠረቶች ማድረግ እንችላለን።
አዲስ ዓመት አዲስ ቀን ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለች ኢትዮጵያን የምንገነባበት አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ተግባር መጀመሪያ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: